Saturday, August 24, 2013

ደብረ ብርሃን ሥላሴ ዘ ጎንደር

                        


ስለ ደብረ ብርሃን ሥላሴ ስናነሣ አፄ ኢያሱ አድያም ሰገድን ማዉሳታችን የግድ ይሆናል፡፡የደብረ ብርሃን ሥላሴን ታሪክ ከአፄ ኢያሱ አድያም ሰገድ ነጥሎ ማየቱ ታሪኩን ያደበዝዘዋል፡፡አፄ ፋሲል ጻድቁ ዮሐንስን፣ጻድቁ ዮሐንስ ደግሞ ዛሬ ታሪኩን በመጠኑ የምናየዉን አድያም ሰገድ ኢያሱን ይወልዳል፡፡እንግዲህ አፄ ኢያሱ የደጋጎቹ ነገስታት ልጅ መሆኑ ነዉ፡፡
 አፄ ዮሐንስ ልጃቸዉን ኢያሱን በትሕርምትና በሥርዓት በገዳም እንዲያድግ በመፈለጋቸዉ አፄ ሠርጸ ድንግል ባቀኑት በአርማጭሆ ወደሚገኘዉ ታላቁ ገዳም ደብረ ሞረና ላኩት፡፡በዚያም በገዳም ዉስጥ የሚሰጠዉን ትምህርት ሥርዓተ ቅዳሴ፣ዜማ ፣ዳዊት አጠናቀዉ ካወቁ በኋላ የገዳሙ ኃላፊዎች ይኼንን አስተምረነዋል ብለዉ ወደ አባታቸዉ ሰደዷቸዉ፡፡አፄ ዮሐንስም‹‹ ሌላስ ምን ተምሯል ብለዉ?››ይጠይቃሉ፡፡ሌላማ ምን እናስተምረዉ ይሏቸዋል የገዳሙ አለቆች፡፡‹‹እንጀራ መጋገር፣የአባቶችን እግርና ልብስ ማጠብ፣ሌላም በገዳሙ ያሉ መነኮሳት የሚፈጽሙትን ተግባር አስተምራችሁታል?››ብለዉ በድጋሚ ቢጠይቁ‹‹ይኼንንማ የጌታችን ልጅ እንዴት እናዛለን ሌላ አርድእት መቼ ታጣና››ይሏቸዋል፡፡ጻድቁ ንጉስም‹‹እንግዲያማ ትዕቢት ነዉ አስተምራችሁ የላካችሁልኝልኝ››ብለዉ መልሰዉ ሰደዷቸዉ፡፡
ከዚያም ኢያሱ በገዳም ያለዉን ሥርዓት አጠናቆ ተምሮ መጣ፡፡አባቱም በቤተ መንግስቱ ዉስጥ ኃላፊነት ይሰጡታል፡፡‹‹‹በገዳሙ የሚሰራዉን ሥራ ሁሉ ንፍሮ በሚበላባቸዉ ቀኖች ንፍሮ፣እንጀራ በሚበላባቸዉ ቀኖች እንጀራ እንዲሆን አድርገህ እንደ ገዳም ሥርዓት ይኼንን ቤተ መንግስት አስተዳድርልኝ›› ብለዉ አባቱ ጻድቁ ዮሐንስ ወራሴ መንግስት ኢያሱን ያዙታል፡፡ኢያሱም እንደታዘዘዉ ቤተ መንግስቱን በገዳም ሥርዓት ማስተዳደር ይጀምራል፡፡በ1674 ዓ.ም ኢያሱ የንግስና መንበሩን ከአባቱ የረከባል፡፡አሁን ኢያሱ ንጉስ ሁኗል፡፡አፄ ኢያሱ በነገሠ በአስራ ሁለተኛዉ ዓመቱ በ1686 ዓ.ም በጎንደር ከተማ የሚገኘዉን የደብረ ብርሃን ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን አስተከለ፡፡በዚህ ዓመት መቃረቢያ ተሠርቶ ቅዳሴ ቤቱ ተከበረ፡፡በበዓሉም ላይ አዲስ ተሹሞ የመጣዉ ግብፃዊ ጳጳስ አቡነ ማርቆስና ለሁለተኛ ጊዜ የተሾመዉ አጨጌ ጸጋ ክርስቶስ ተገኝተዋል፡፡በዓሉ በተከበረበት ዕለት አፄ ኢያሱ በትልቅ ፈረስ ላይ ተቀምጦ ሻምላ መዝዞ ታቦቱን አጅቧል፡፡ወደ መቃረቢያዉ ሲደርስ ከፈረሱ ወርዶ ታቦቱን አክብሮ ከመቃረቢያዉ አገባዉ፡፡;እዚህ ላይ አፄ ኢያሱ ሥልጣነ ክህነት ይኑረዉ አይኑረዉ የተገኘ ማስረጃ ስለሌለ እንዲህ ነዉ ማለት አልተቻለም፡፡ክህነት ነበረዉ የሚሉ ግን ታላላቅ ሊቃዉንት ቅኔ አበርክተዋል፡፡ዓቃቤ ሰዓት ጥበበ ክርስቶስ መወድስና ኩልክሙ ምናኔ ዓለም የነበረዉ አባ ቀዉስጦስ ዕጣነ ሞገር ተቀኝተዋል፡፡ካእነዚህ ቅኔዎች አንዳቸዉም በዘመን ታሪክ ዉስጥ ተመዝግበዉ አልተገኙም፡፡አፄ ኢያሱ ታቦቱን አክብሮ ስለመግባቱ በዘመኑ ተገጠመ የተባለ የአማርኛ ግጥም ይህንን ይመስላል፡፡
                            ወዴት ሄዶ ኑሯል ሰሞነኛዉ ቄሱ
                            ታቦት ተሸከመ ዘዉድ ትቶ ኢያሱ
                            የተሸሸገዉን የ አባቱን ቅስና
                             ገለጠዉ ኢያሱ ታቦት አነሳና
                            አየነዉ ኢያሱን ደብረ ብርሃን ቁሞ
                           ሰዉነቱን ትቶ መልአክ ሆነ ደግሞ
                         ሥላሴን ቢሸከም ኢያሱ ገነነ
                         ከ አራቱ ኪሩቤል አምስተኛዉ ሆነ፡፡
በዚህ ደብር መጀመሪያ የተሸመዉ ቀዉስጦስ ነበረ፡፡የደብሩም የመጀመሪያ የማዕረግ ስም ሊቀ ካህናት ነበር፡፡ወዲያዉ ተለዉጦ መልአከ ብርሃን ሁኗል፡፡ቀዉስጦስ ያረፈዉ በ1716ዓ.ምበ85 ዓመት ዕድሜዉ ነበር፡፡እስከዚያዉ ድረስ በሹመቱ ቆይቶ እንደሆነ የተጻፈ መረጃ አልተገኝም፡፡የተቀበረዉ ግን እዚያዉ ደብረ ብርሃን ሥላሴ ቤ/ክ ቅጽር ግቢ ዉስጥ መሆኑ ይታወቃል፡፡ታቦተ ህጉም በመቃረቢያዉ ዉስጥ ለሁለት ዓመት ቆይቶ የዋናዉ ሕንፃ ቤ/ክ ሥራ ጀመረ፡፡በ1688ዓ.ም የህንፃዉ ሥራ ሲጠናቀቅ ወደ አዲሱ ህንፃ ገብቷል፡፡ቤተ ክርስቲያኑ የተሰራበት እንጨት በጣም ትልልቅ ነበር፡፡በዚያን ጊዜ በምን መጓጓዣ እንዳመጡት ላስተዋለ ያስገርማል፡፡እንጨቱ የመጣዉ ግማሹ ከዘጌ ነዉ ሲል የተቀረዉ ደግሞ ከአርማጭሆ እንደሆነ ይነገራል፡፡የቀድሞዉ ህንፃ ክብ ሲሆን ሦስት መቅድስ ነበረዉ፡፡የበሩ ሳንቃዎች ሲከፈቱ አይታዩም ተሸከርክረዉ ወደ ዉስጥ ግድግዳዉ ነበር የሚገቡት፡፡
                                         ስያሜ
አፄ ኢያሱ ቤተ ክርስቲያኑን ካሰሩ በኋላ ታቦተ ጽዮንን ወደ ጎንደር ለማስመጣት ወደ አክሱም ጉዞ አድርገዉ ነበር፡፡በተለያዩ ምክንያቶች ለማምጣት ሳይቻላቸዉ ቀርቷል፡፡በዚህም ቅር ተሰኝተዉ የአክሱም ጽዮን አካባቢ ሕዝብ ሦስት ቀን ግብር ከልክሏቸዋል፡፡ከዚያም አብረዋቸዉ የተጋበዙት አባ ስብሐት ለአብ የሚባሉ ሰዉ ሕዝቡ በርሃብ ሊያልቅ ሲል ታቦተ ጽዮንን ማምጣት ባይሳካልን ለምን ታቦተ ሥላሴን አናስገባም አሏቸዉ፡፡በዚሁ ተስማምተዉ ታቦተ ሥላሴ እንዲገባ አድርገዋል፡፡የአክሱም ታቦተ ጽዮንም ለደብረ ብርሃን ሥላሴ ግብር እንድታስገባ ግብር ጥለዉባት ተመልሰዋል፡፡
አፄ ኢያሱ ወደ ሸዋ ደብረ ብርሃን ተጉዘዉ ሊቃዉንቱንና ባላባቱን ጠይቀዉ ደብረ ብርሃን የሚለዉን  ስም ለመሰየም ፈቃድ ሲያገኙ ብዙ ወቄት ወርቅ ሰጥተዉ ተመለሱ፡፡ይኼነን ስያሜ የመረጡበት ምክንያት ቦታዉ ብርሃን የወረደበት በመሆኑ በሁኔታዉ ተማርከዉ እንደሆነ ይነገራል፡፡
                       በጠላት ወረራ ጊዜ
ድርቡሽ የጎንደር ከተማን ሲያቃጥል ሕዝቡ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ በመሰባሰብ ጸሎተ ምህላ ያደርግ ነበር፡፡ሰማዩም በጉምና በጢስ ይሸፈናል፡፡ቤተ ክርስቲያኑ እንዲጠፋ የፈለጉ ሰዎችም‹‹ደብረ ብርሃን ስላሴ ካልተቃጠለና ካልጠፋ ጎንደር እንዳልጠፋች ይቆጠራል›.በማለት ለድርቡሾች መንገድ እየመሩ የመጡበት ጊዜ እንደነበር የ አካባቢዉ ሰዎች ይናገራሉ፡፡ድርቡሾች በሩን ለመስበር የተቻላቸዉን ቢያደርጉም ሳይሆንላቸዉ ይቀራል፡፡እንጨት ሰብስበዉ አቃጥለዉ ለመግባት ሲሞክሩ በበሩ ላይ የተሳለዉ የሳንቃዉ ቅ/ሚካኤል ሥዕል ሰይፍ እንደመዘዘ ለህዝበ ክርስቲያኑ ሳይታይ ለእነርሱ ብቻ ይታያቸዋል፡፡በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር ያለዉ ከዚህ ቦታ ነዉ እንዳትነኩ ብለዉ ተመልሰዉ ጥለዉት  እንደሄዱ የሚነገር ታሪክ አለ፡፡በቤተ ክርስቲያኑ ያሉ አባቶች ይኼንን ሥዕል ቄስ ካልሆነ ዲያቆን እንኳን እንዳይነካ በማለት ተከብሮ በዓመት ዉስጥ ሁለት ጊዜ ብቻ ማለትም የሰኔ እና የኅዳር ሚካኤል ዕለት ብቻ እንዲገለጥ ወስነዋል፡፡
  አፄ ኢያሱ የዘመነ መንግስቱ ፍጻሜ በተቃረበበት ወቅት የሥላሴን ቤተ ክርስቲያን በ1685 ዓ/ም በሥዕል ማሰራትና ማስጌጥ ጀምሮ ነበር፡፡ደብሩ በጊዜዉ ከከተማ ወጣ ያለ በመሆኑና በእግዚአብሔር ተአምር ከድርቡሽ ወረራ ከመቃጠል ድኗል፡፡ነገር ግን የዘመኑ ታሪክ እንደሚያወሳዉ በ1699 ዓ.ም መብረቅ ቤተ ክርስቲያኑን እንዳቃጠለዉ ይጠቀሳል፡፡ይህም በከፊል ይሁን በሙሉ የተብራራ ነገር የለዉም፡፡የደብሩ አስተዳዳሪ እንደሚገልጹትም አፄ ኢያሱ ያሰራዉ ቤተ ክርስቲያን ፈርሶ ልጅ ዳዊት/ሣልሳይ/እንደገና እንዳሰራዉም ይገልጻሉ፡፡በዉስጡ የተሳሉ ስዕሎችም በጊዜዉ የተሳሉ መሆናቸዉን ይገልጻሉ፡፡ሥዕሎቹን በጊዜዉ የነበረዉ ጸሐፌ ትዕዛዝ ሐዋርያተ ክርስቶስ ዓለም ከተፈጠረ አንስቶ ወደፊትም እንዲህ ያለ ሥዕል አይኖርም ሲል መስክሯል፡፡ሥዕሎቹም ትልልቅ ዓይኖች ክብ ፊት ያላቸዉ የጎንደር ሥዕሎች መታወቂያ ናቸዉ፡፡ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረ ጊዜ የቤተ ክርስቲያኑን አካባቢ ምሽግ አድርጎት ነበር፡፡ጠላት በጎንደር ስድስት ዓመት ያክል ሲቀመጥ ቦምብ ከ አየር ላይ ቢወርድበትም ቤተ ክርስቲያኑ ከቃጠሎ መትረፍ ችሏል፡፡ጣሊያን ይህ ተ አምር ስላስገረመዉ የቤተ ክርስቲያኑን ክዳን ቀድሞ መምህር ገ/እግዚአብሔር በተባሉ የቤተ ክርስቲያኑ አለቃ/በኋላ አቡነ መርቆርዮስ በሐረር በነበሩ ጳጳስ ጠያቂነት በሸክላ አለበሰዉ፡፡በኋላ በ1957 ዓ.ም አፄ ኃይለ ሥላሴ ቆርቆሮ አስቀይረዉ ዙሪያዉን አጠናክረዉ አሠሩለት፡፡በዚህ ሁኔታ እስከ 1964 ዓ/ም ቆየ፡፡ባሕል ሚኒስተርም ጥንታዊነቱን መልቀቅ የለበትም በማለት በቆርቆሮዉ ላይ የቀድሞዉን ሣር አለበሰዉ፡፡
በቤተ ክርስቲያኑ ዙሪያ የ እንቁላል ግንብ በመባል የሚታወቁ ቤቶች አሉ፡፡በ አፄ ኢያሱ ዘመን  በ12 ሐዋርያት አምሳያ በዚያዉ ዘወትር የሚቀመጡ ወደ ከተማ የማይወጡ መቁነን በዚያዉ እየተሰጣቸዉ ሰዓቱን እየከፋፈሉ የሚያጥኑ 12 መነኮሳት ይቀመጡበት ነበር፡፡በአሁኑ ሰዓት ብዙዎቹ እየፈራረሱ ይገኛሉ፡፡ቀድሞ በሕል ሚኒስተር ነበር ለጥገናዉ የሚንቀሳቀሰዉ፡፡አሁን ግን የ አካባዉ ነዋሪዎች ለጥገና የሚስፈልገዉን ገንዘብ በመሰባሰብ ኮሜቴ አዋቅረዉ የጥገና ሥራዉን እያንቀሳቀሱት ይገኛሉ፡፡
በደብረ ብርሃን ሥላሴ ቀድሞ 170 በላይ ካህናት ያገለግሉ ነበር ተብሎ ይገመታል፡፡ዛሬ ግን ከ25-30 ቢደርሱ ነዉ፡፡ደሞዛቸዉም ይህንን ያህል በቂ የሚባል አይደለም፡፡ቅዳሴ እሁድ፣በባዓላት ፣በዐብይ ጾም እሑድ፣በጾመ ፍልስታ የ እመቤታችን ክብረ በ ዓል ዕለት ይደርሳል፡፡በቤተ ክርስቲያኑ ያብነት ትምህርት/ቅኔ/ይሰጣል፡፡150-200የሚሆኑ ደቀ መዛሙርት ይማራሉ፡፡ቁጥራቸዉ ከዚህ የሚጨምርበትም የሚቀንስበትም ጊዜ አለ፡፡ይኼንን ጥንታዊና ታሪካዊ ቤተ ክርስቲያን የቀድሞ ይዘቱንና ቅርጹን ሳይለቅ እንደተጠበቀ ለትዉልድ እንዲተላለፍ ለማድረግ ምዕመናን አቅማቸዉ የፈቀደዉን ሁሉ ማድረግ ቢችሉ መልካም ነዉ፡፡ስለ ደብረ ብርሃን ስላሴ ያገኘነዉ መረጃ ይኼንን ይመስላል፡፡ የቤተ ክርስቲያኑ ታሪክ ሲነሣ ስሙ ስለሚወሳዉ ስለ አፄ ኢያሱ የተነገረለትን ጠቅሰን ብናጠቃልስ፡፡አንድ ጊዜ አፄ ኢያሱ ደብረ ብርሃን ሥላሴ ሄዶ ሳለ ክፍለ ዮሐንስ የተባለ ሊቅ ሲፀልይ አግኝቶ ከኪሱ ያገኘዉን ወርቅ አዉጥቶ ወረወረና ሊቁን ሳያስበዉ መታዉ፡፡በዚህ ጊዜ ክፍለ ዮሐንስ የሚከተለዉን ጉባኤ ቃና ወዲያዉ ሰጠ፡፡
                             በእስጢፋኖስ አእባን እመኅልቁ

                             ዘበጣኒ ኢያሱ በወርቁ/ድንጋዮች በእስጢፋኖስ ላይ ቢያልቁ ኢያሱ መታኝ በወርቁ/
                                            ወስብሐት ለእግዚአብሔር
 ምንጭ የቃል አስረጅ የደብሩ አስተዳዳሪ
የ አማርኛ መዝገበ ቃላት ሥርግዉ ሐብለ ሥላሴ/ዶ/ር/

           

Tuesday, July 23, 2013

ግዕዝ ይማሩ - ክፍል አንድ

ክፍል ፩
መፍቀርያነ ግእዝ /ስለ ግእዝ እነማን አጠኑ/
መፍቀርያነ ግእዝ ስንል ስለ ግእዝ ያጠኑ፤ ጥናትና ምርምር ያደረጉ፤ ግእዝን የተማሩ የተመራመሩ ያወቁ ያሳወቁ፤ የጻፉ ፣ ያጻፋ ለማለት ተፈልጎ ነው፡፡
የግእዝ ቋንቋን ከፊደላቱ ጀምሮ ቃላቱን ሰዋሰውን /ዘርና ነባሩን፣ ግስና አገባቡን/፣ አንቀጹን ቅኔውን እንዲሁም ሌሎች የግእዝ ዘርፎችን የውጭ ሀገርና የሀገር ውስጥ ምሁራን የቋንቋ ሊቃውንት ሌሎችም ከተሰማሩበትና ከዋና የሥራ መስካቸው በመለየት ዘመናቸውን አሳልፈውበታል፤ ተራቅቀውበታልም፡፡ 1 እነዚህንም ምሁራን በዘርፍ በዘርፍ ስንመለከታቸው በሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል፤ የውጭ ሃገር ምሁራንና የሃገር ውስጥ ሊቃውንትና ምሁራን በማለት፡፡
ሀ. ከውጭ ሀገር ምሁራን
፩. ሊቀ ካህናቱ አዛርያስ እና ከሱ ጋር ተከ ለው የመጡት ፫፻፲፰ቱ ሌዋውያን ካህናት/፱፻፹ ቅ.ል.ክ/፡-እነዚህ መምህራን ቀዳማዊ ምኒልክ ታቦተ ጽዮንን ከእስራኤል ወደ ኢትዮጵያ ይዞ ሲመጣ አብረው የመጡ ሊቃውንት ሲሆኑ የግእዝን ቋንቋ ተምረው ብሉይ ኪዳንን ለመጀመሪያ ጊዜ ከእብራይስጥ ወደ ግእዝ የተረጎሙ ናቸው፡፡ 2 እነዚህም ሊቃውንት መጻሕፍትን በመተርጎማቸው በገድለ ቀውስጦስ ላይ ንጉሥ ዘሩባቤል /ከባቢሎን ምርኮ በኋላ/ መጻሕፍተ ብሉያትን ጽፈህ ላክልኝ ብሎ ለኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ልኮበታል፡፡ 3  
፪. አባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን /በአብርሃ ወአጽብሃ ዘመን/፡- አስቀድሞ መጠሪያ ስሙ ፍሬምናጦስ ነበር፡፡ ኋላ በሊቁ ቅዱስ አትናቴዎስ ፓትርያርክ ዘእስክንድርያ አማካይነት በ፫፻፴ ዓ.ም ‹‹ አባ ሰላማ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዘኵላ ዘኢትዮጵያ ›› ተብሎ ተሹሞ መጣ፤ ኢትዮጵያውያኖችም ከሳቴ ብርሃን የሚለውን ስም አወጡለት፤ ገና ጳጳስ ሳይሆን ከወንድሙ ከአድስዮስ ጋር ወደ ኢትዮጵያ እንደመጣ ከሊቀ ካህናቱ እንበረም /ኋላ ሕዝበ ቀድስ/ ዘንድ ሙራደ ቃል በምትባል ቦታ ግእዝን ተምሯል፡፡ 4 የሐዲስ ኪዳንን እና የሥርዐተ ቤተክርስቲያንን ጽሑፎች  እንደተረጎመም ይታመናል፡፡ 5  
፫. ተሰዓቱ ቅዱሳን፡- ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ቀድሞ ፍሬምናጦስ በተማረባት ሙራደ ቃል በምታባል ቦታ ግእዝን ተምረዋል፡፡ በዚህም መሠረትነት የግእዝን ቋንቋ በመማር በማስተማር በመጻፍ በማጻፍ፣ መጻሕፍትን በመተርጎምና በማስተርጎም ተሳትፈውበታል፡፡ 6

፬. ሊቀ ካህናት እንበረም (ኋላ ሕዝበ ቀድስ)//፡- ከአብዩድ እና ከሌሎች የኢትዮጵያ ሊቃውንት ጋር በመሆን ከ፬፻፴፭-፬፻፶ ዐ.ም ለ፲፭ ዓመታት ያህል በግእዝ ላይ ከፍተኛ ጥናት አካሂዷል፤ አባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃንን እና ወንድሙን አድስዩስን ሙራደ ቃል በምትባል ቦታ ግእዝን አስተምሯል፡፡                                                                                              
፭. አባ ካልኣይ ሰላማ (መተርጕም ሰላማ) /ከ፲፫፻፵፩-፲፫፻፹/ ፡- ለአርባ ዓመታት ኢትዮጵያን በሊቀ ጵጵስና የመራ ሲሆን ዜግነቱን ኢትዮጵያዊ ነው የሚሉም አሉ፡፡ ብዙ መጻሕፍትን ወደ ግእዝ ተርጕሟል ለአብነትም ሐዲስ ኪዳንን ከዐረብኛ ወደ ግእዝ ተርጒሟል በተጨማሪም ግብረ ሕማማትን፣ ገድለ አበከረዙን፣ ገድለ አዝቂር፣ ድርሳነ ገላውዴዎስ፣ ፊልክስዩስ፣ ገድለ ይስሐቅ፣ ገድለ ዮስጦስ፣ ገድለ ኖብ/አባ ኖብ ድንግል/፣ ድርሳነ ያዕቆብ ዘኢየሩሳሌም፣ ድርሳነ ያዕቆብ ዘሥሩግ፣ አስተርእዮቱ ለእንባቆም፣ ለሃ ማርያም፣ መጸሐፈ ግንዘት ሲገኙበት እርሱ እያስተባበረ ካጻፋቸው መጻሕፍትም መካከል ቄርሎስና ፊሳልጎስ ይገኙበታል፡፡ 7 
 
 1. ትንሣኤ ግእዝ፣ ፳፻፪፣ ፪
 2. መጽሐፈ ምሥጢር ፣ የልደት ምንባብ ፤ መጻሕፍተ ሰሎሞን ወሢራክ መቅድም
 3. አለቃ አስረስ የኔሰው፣ ትቤ አክሱም መኑ አንተ፣ ፲፱፻፶፩፣ ፻፶፱ ፣ ገድለ ቀውስጦስ
 4. አለቃ አስረስ የኔሰው፣ ፲፱፻፶፩፣ ፪፻፷፩
 5. ሐመረ ጽድቅ፣ ፲፱፻፺፭፣ ፲፭
፮. እጨጌ እንባቆም /፲፬፻-፲፭፻፶፫/:-በግእዝ ቋንቋ መጻሕፍትን ጽፏልቅዱሳት መጻሕፍትንም ወደ ግእዝ መልሷል፡፡ ለአብነትም አንቀጸ አሚንን ራሱ ጽፏል፤ መጽሐፈ በርልአምን፥ መጽሐፈ ተልሚድን ከዐረብኛ ወደ ግእዝ  ተርጉሟል፤ አቡሻኽርን በመምሕር ሰሊክና በእጨጌ አበሞ አማካይነት ተርጕሟል፡፡ 8
  ] የቋንቋውን ሥርዐተ ሰዋስው ለማጥናት እና የቋንቋውን የትመጣ ለመመርመር የደከሙት ግን  ፲፫ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ከእነዚህምሁራን ተዋቂዎቹና ዋነኞቹ፡-                                                       
፯. ኢዮብ ሉዶልፍ :- ዜግነቱ ጀርመናዊ ሲሆን « የመጀመሪያውን» የግእዝ ሰዋስው ያሳተመው በአባ ጎርጎርዮስ ርዳታ .. በ፲፮፻፷፩ ዐ. ሲሆን በ፲፮፻፺ . ደግሞ የአማርኛ ሰዋስውን በአጭሩ ጽፎ አሳትሟል፡፡ በአንዳንዶች ዘንድ የመጀመሪያው የግእዝ ሰዋስው በሮም አውሮፓ// ተሰራ ተብየሚታመነው በ፲፮፻፴፰ ዐ. የተሰራው .ወመር ሥራ ሲሆን ግእዝን በተመለከተ መጻሕፍትን ለማሳተም ግን በ፲፭፻፲፫. የታተመው ፑተን /የፑትከን/ መጽሐፍ ቀዳማዊ መሆኑ ይታወሳል፡፡ እንዲሁም በ፲፭፻፶፪ ዐ. የታተመው የግእዝ ሰዋስው መልክዕ ገላጭ ማሪያነስ ቪቶሪ /ቪክቶሪየስ/ ነው፡፡ ከፑተን እና


ከማሪያነስ ቪቶሪ ግን የዐረብኛ እና የእብራይስጥ ቋንቋ እውቀቱን የተጠቀመበት የኢዮብ ሉዶልፍ ሥራ የተሻለ ነበር፡፡ 
፰. ኦውገስት ዲልማን /፲፰፻፳፫-፲፰፻፺፬/፡-  ዜግነቱ ጀርመናዊ ሲሆን የግእዝ ሰዋስውን በ፲፰፻፶፭ ዐ.ም፤ የግእዝ መዝገበ ቃላትንም በ፲፰፻፶፭ ዐ. በላቲን/ ያለፉትን መዛግብት በመጠቀም ያዘጋጀው ሥራ በግእዝ የተሰማሩ ሊቃውንትንና ደቀመዛሙርትን በመርዳት የሚያኽለው የለም፡፡ ብዙዎችን ይጥቀም እንጂ ዲልማን የግእዝን የአነባበብ ሥርዐት ለማስቀመጥ ያደረገው ጥረት ስኬታማ ነበር ለማለት እንደማይቻል ኹሉ የግእዝን ቀዳማይ አንቀጽ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ለማስረዳት የተጠቀመበት የንዑስ አንቀጽ ትርጕም ግን እንደ ድክመት ሊታይ የሚችል ነው፡፡
    ለጀማሪ የግእዝ ተማሪዎች ሊረዱ የሚችሉ መጻሕፍትን ከሠሩት ከፕሪቶሪየስ እና ቼል ጀምሮ ኮንቲሮሲኒ ሊትማን ሊኦኔል ቤንደር(ስለ ግእዝ ፊደላት)፣ሚትወች (ስለ ሥርዐተ ንባብ) እና የተሻለ የግእዝ መዝገበ ቃላት እስካዘጋጀው ወልፍ ሌስሎው ድረስ በግእዝ ቋንቋ ላይ የተደረጉ ምርምሮች አበረታች ነበሩ፡፡ 9 

. ከሀገር ውስጥ ሊቃውንትና ምሁራን
፩. ሊቁ /ያሬድ /፭፻፭-   /- ለግእዝ ቋንቋ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረገ አባት ነው፡፡ ካደረጋቸው አስተዋጽዖ መካከልምቱን የዜማ መጻሕፍት /ድጓ፣ ጾመ ድጓ፣ ምዕራፍ፣ መዋስዕት፣ ዝማሬ/ እና አንቀጸ ብርሃንን በግእዝ ቋንቋ ዓይነት የዜማ ስልት ማለትም በግእዝ በዕዝልና በአራራይ ደርሷል፡፡ እንደሁም በሰሜን ተራሮች ከራስ ዳሽን አጠገብ በሚገኘው በደብረ ሃሌ ሉያ ተራራ ላይ፣ … እንዲሁም በተለያዩ የሃገራችን ክፍሎች መንፈሳዊ ትምህርትን በግእዝ አስተምሯል፡፡
፪. ሊቁ /አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ (ኢትዮጵያዊው ቄርሎስ) /፲፫፻፶፯-፲፬፻፲፯/- ከ፵ በላይ ቅዱሳት መጻሕፍትን የጻፈና የወርቃማ ዘመን ወርቅ ደራሲ እስከመባል የደረሰ ሲሆን መጻሕፍቶቹን ሁሉ በግእዝ ቋንቋ በመጻፍ ለግእዝ ቋንቋ ከፍተኛ አስተዋጽዖ  አድርጓል፡፡ በተለይም ዕንዚራ ስብሐት  በተባለው መጽሐፉ በሁሉም የግእዝ ፊደላት
      

 6. መ/ር ዘርአዳዊት አድሐና (የቃል ትምህርት)
     7. ዶ/ር ሥርግው ኃብለ ሥላሴ ቅጽ ፊ ፵፱
     8. ሐመረ ጽድቅ፣ ፲፱፻፺፭፣ ፲፭
     9. ትንሣኤ ግእዝ፣፳፻፪፣ ፪
 


 (በ፪፻፪ቱም ፊደላት) እመቤታችንን በግጥም አመስግኗታል፤ በግእዝ ሥነ ጽሑፍ በኩልም ብራን ካሌዎን ለተባለ ካቶሊካዊ በመጽሐፈ ምሥጢር «በተጠየቅ ልጠይቅ» አካሄድ ግሩም በሆነ የግእዝ ሥነ-ጽሑፍ አጻጻፍ መልሶለታል፡፡
. ከነገሥታት ወገንም አጼ አብርሃ ወአጽብሐ ግእዝን ብሔራዊ ቋንቋ በማድረግ፤ አጼ ዘርዓ ያዕቆብ /፲፬፻፳፮-፲፬፻፷ ዐ./- የተለያዩ መጻሕፍትን በግእዝ ቋንቋ በመጻፍና ሌሎችም እንዲጽፉ፤ መጻሕፍትን እንዲተረጕሙ በማድረግ አስተዋጽዖ አድርገዋል፡፡ 
፬. አእጋረ ፀሐይ ተክለሃይማኖት- የፊደላት ቅርጽን በየገዳማቱ እየጻፈ እንዳይጠፉ ያደረገ ታላቅ አባት ነው፡፡ 2
፭. እነ ዮሐንስ ገብላዊ /፲፬፻፳፯-፲፬፻፷ ዓ/ም/:-ቅኔን ከነቤት መምቻውና ከነምሥጢሩ አስፋፍቶ በማስተማር/
፮. ሠምራ አብ- ዘአምላኪየ፣ ዋይዜማ፣ ዘይእዜ፣ ግእዝና እዝል ክብር ይእቲ እንዲሁም ግእዝና እዝል ዕጣን ሞገር የተሰኙትን ቅኔያት በመድረስ፤
፯. ድድቅ ወልደማርያም፡- በ፲፭፻፳፪ ዐ.ም ግራኝ መሐመድ በኢትዮጵያ በተነሣ ጊዜ ቅኔን አገባብን እና ዕርባ ቅምርን ይዞ ለትውልድ በማሰተላለፉ፤
፰. ድድቅ- የቅኔ ጉባኤን በማስፋፋት ሰባት ዓይነት የአግባብ አዋጅና አገባብ፣ ሰባት ዓይነት የዕርባ ቅምር አዋጅና ዕርባ ቅምር በማስተማር፤
፱. ሊቁ ክፍለ ዮሐንስ- በግእዝ ቅኔያት ላይ እጅግ በመራቀቅ፣
፲. አለቃ ገብረ ሃና- በግእዝ ቅኔያት ላይ እጅግ በመራቀቅ፣ የተክሌን አቋቋም በግእዝ ቋንቋ በመድረስ፤   
፲፩. / አክሊሉ- የቅኔ ዜማ ልክን በደንብ መስመር በማስያዝ
፲፪. ወላዴ ሊቃውንት መልአከ ምሕረት ጥበቡ ታዬ- ከመምህራቸው ከመ/ አክሊሉ የተማሩትን ለብዙ ሊቃውንት በማስተማር፡፡ የቅኔውን ትምህርት ሲያስፋፉ አብሮም የግእዝ ቋንቋ እንዲስፋፋ አስተዋጽዖ አድረገዋል፡፡ 3
       ] ለግእዝ ሰዋሰው መጠበቅ፣ ለሥነ ጽሑፍ ዕድገቱ መዳበር በዋናነት ተጠቀሽ የሚሆኑት የኢ//// በቃልም ይሁን በመጽሐፍ ለቋንቋው ሥርዐተ ሰዋሰው እና ዕሤታት መጠበቅ በሀገር መዓዛዎቹ በሊቃውንቷ እና በጉባኤ ቤቶቿ በተለይም በቅኔ ጉባኤ ቤት ውስጥ ዓይናማ/ሊቅ/ የሆኑ መምህራን ያደረጉትና እያደረጉ ያሉት አስተዋጽኦ እና ተጋድሎ ሕያውና ታላቅ ነው፡፡


ከዚህም መካከል ከላይ የጠቀስናቸው ሲገኙበት በመጽሐፍ ዝግጅት ደግሞ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ካደረጉት    መካከል ዋና ዋናዎቹ፡-
ከቀደምቶቹ፡-
፩. አባ ተክለማርያም ወልደ ሰማሃራይ
   
 8. ሐመረ ጽድቅ፣ ፲፱፻፺፭፣ ፲፭
 9. ትንሣኤ ግእዝ፣፳፻፪፣ ፪
 3. መ/ር ገ/ሕይወት ፈንታሁን፣ ሥርዐተ ትምህርተ ቅኔ ዘግእዝ፣ ፳፻፩
፪. አባ ያዕቆብ ገብረ ኢየሱስ
፫. አለቃ ታየ
፬. አለቃ ክፍለ ጊዮርጊስ /፲፰፻፲፯-፲፱፻/- «መጽሐፈ ሰዋሰው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ» የሚለውን መጽሐፍ ረቂቁን በማዘጋጀት፤
፭. አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ /፲፰፻፷፬-፲፱፻፴፮/፡- «መጽሐፈ ሰዋሰው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ» የሚለውን መጽሐፍ ለመጽሐፍ ሕትመት እንዲሆን በማዘጋጀት፣ በተጨማሪም መዝገበ ፊደል ሴማውያት፣ አበገደ ፊደልና፣ ፊደላዋርያ» በሚባሉ መጻሕፍቶቻቸው፤
፮. አለቃ ደስታ ተክለወልድ /፲፰፻፺፫-፲፱፻፸፯/- «መጽሐፈ ሰዋሰው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ የሚለውን መጽሐፍ በማሳተም» እንዲሁም «ረብሐ ስም ወአንቀጽ» በሚል መጽሐፋቸው፡፡
፯. አለቃ አስረስ የኔሰው፡- የግዕዝና የአቡሻኽር ሊቅ ሲሆኑ «ትቤ አክሱም መኑ አንተ» እንዲሁም «የካም መታሰቢያ» በሚባሉ መጽሐፍቶቻቸው፡፡
፰. ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ መስቀል፡- «መጽሐፈ ቅኔ» በሚል መጽሐፋቸው፡፡ 
፱. መልአከ ብርሃናት አድማሱ ጀንበሬ- «ዝክረ ሊቃውንት ክፍልእና ፪» በሚል መጽሐፋቸው፡፡
፲. መምህር ይኄይስ ወርቄ- «ንባብ ወትርጓሜ ዘቅኔያት አዕማደ ምሥጢራት» በሚል መጽሐፋቸው፡፡ 



ከቅርቦቹ፡-
፩/ ዜና ማርቆስ እንዳለው- «የግዕዝ ቋንቋ መግቢያ፣ ጥንታዊ ግእዝ በዘመናዊ አቀራረብ፣ ቅኔ ለወጣቶች፣ እና ግዕዝ ቋንቋ ላራተኛ ክፍል» በሚባሉ መጻሕፍቶቻቸው፡፡
፪. / ያሬድ ፈንታ- «ፍኖተ ግእዝ» በሚል መጽሐፋቸው
፫. መሪጌታ ልሳነ ወርቅ ገብረ ጊዮርጊስ- «ጥንታዊ ሥርዐተ ማኅሌት ዘአቡነ ያሬድ ሊቅ» በሚል መጽሐፋቸው፡፡
፬. / ኢሳይያስ ዓለሜ እንግዳ- «የግእዝና የዐረብኛ ቃላት ተዛምዶ /ግንኙነትበሚል መጽሐፋቸው፡፡ 
፭. አፈወርቅ ዘውዴ- «ሀገረ መጻሕፍት» በሚል መጽሐፋቸው
፮. / ዘርአዳዊት አጽሐና- «መርኆ ሰዋስው ዘልሳነ ግእዝ» በሚል መጽሐፋቸው፡፡
፯. ሊቁ መልአከ አርያም ይትባረክ መርሻ- «የግእዝ አገባብና የቅኔ መንገዶች» በሚል መጽሐፋቸው፡፡
. ሊቃ ሊቃውንት ያሬድ ሽፈራው- «መጽሐፈ ሰዋሰው ወግስ መርኆ መጻሕፍት» በሚል መጽሐፋቸው፡፡
፱. ንቡረ እድ ኤርምያስ ከበደ ወልደ ኢየሱስ፡- «ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት /ክፍል ፩-፫/» እንዲሁም «ኢትዮጵያ የዓለሙ መፋረጃ» በሚባሉ መጻሕፍቶቻቸው፡፡
፲. አባ ተክለ ሀይማኖት «ቀላል የግእዝ ቋንቋ መማሪያ» በሚል መጽሐፋቸው፡፡
፲፩. ክንፈ ርግብ አታለል
፲፪. ሊቀ ኅሩያን በላይ መኮንን- «ሕያው ልሳን» እንዲሁም «ትንሣኤ» በሚባሉ መጻሕፍቶቻቸው
፲፫. / /ዮሐንስ /ማርያም- «በቀላሉ የግእዝ ቋንቋ መማሪያ» በሚል መጽሐፋቸው፡፡
፲፬. / ፍሰሐጽዮን ካሣ- «መርኆ አዳም ወግዕዝ» በሚል መጽሐፋቸው፡፡ 
፲፭ . / ታምር ገብረመስቀል- «የግእዝ ቋንቋ ፈደላት የተናጠል አገባብና ሥርዓተ አጻጻፍ መዝገበ ቃላት /፩ኛ/» በሚል መጽሐፋቸው፡፡
፲፮. / ለይኩን ብርሃኑ፡- «የግዕዝ መማሪያ» በሚል መጽሐፋቸው
፲፯. መሪጌታ አፈወርቅ
፲፰. የመናገሻ ገነተ ጽጌ /ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ሰንበት /ቤት፡- «ፍሬ ግእዝ» በሚል መጽሐፋቸው፡፡
፲፱. / ደሴ ቀለብ /ማኅበረ ቅዱሳን/- «ትንሣኤ ግእዝ» በሚል መጽሐፋቸው ይታወቃሉ፡፡
]ምንም እንኳን በመጽሐፍ መልኩ ባያሳትሙም በሽት መልክ /Handout/ እያዘጋጁ በአሁኑ ጊዜ ለግእዝ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽዖ ካደረጉትና እያደረጉ ከሚገኙት መካከል፡-
፩. / ረዘነ ኪዳነ- የከሳቴ ብርሃን መንፈሳዊ ኮሌጅ የግእዝ ቋንቋ መምህር፡፡
፪. / / ሲሳይ ደመቀ፡- ግእዝን በጎንደር ለሚገኙ የግቢ ጉባኤያት፣ ለሰንበት /ቤቶች በማስተማር፤ ግእዝን በጎንደር ዩኒቨርሲቲ እንደ ጋራ የትምህርት መስክ /common course/ በማስተማር ላይ ያሉ፡፡ 
፫. / እንባቆም- በደ/ብርሃን ለሚገኙ የግቢ ጉባኤያት የግእዝ መምህር
፬. ሊቀ ጠበብት ይባቤ- በፍኖተ ሰላም ከተማ በግላቸው ኰሌጅ ውስጥ ግእዝን እንደ አንድ ቋንቋ እያስተማሩ የሚገኙ፡፡
፭. / መንግሥቱ ሐጋዚ- በማይጨው ለሚገኙ ተማሪዎችና በአካባቢው ለሚገኙ ምዕመናን ግእዝን በማስተማር ላይ ያለ፡፡
፮. የልሳነ ግእዝ ወዳጆች ማኅበር- በአ/አበባ ለሚገኘው የማኅበረ ቅዱሳን የአዲስ አበባ ማዕከል፣ በሐመር መጽሔት እና በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች እንዲሁም በአንዳንድ ሰንበት ትምህርት ቤቶች ግእዝን በማስተማር ላይ ያሉ፡፡
፯. የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ኰሌጅ  የግእዝ ዲፕሎማ ተማሪዎች፡- በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ግእዝን በቋንቋ ደረጃ ለብቻው በዲፕሎማ እየተማሩ የሚገኙ ተማሪዎች ሲሆኑ ለወደፊቱ ግእዝን በማሳደግ ተስፋ የተጠላባቸውም ናቸው፡፡
፰. / ባዬ ይማም- አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለመጀመሪያ ጊዜ የቀንየሥነ ልሳን ጥናት /Philology/ እንዲጀመር ያደረጉ፡፡ 
፱. አኵስም፣ ጎንደርና ደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ- ግእዝ ቋንቋ እንደ አንድ የትምህርት መስክ/Department/ በመክፈት ትምህርቱ እንዲስፋፋ እያደረጉ ያሉ ናቸው፡፡ 



Oval: ክፍል ፪

 


ግእዝ የማን ቋንቋ ነው /አይቴ ብሔሩ ለግእዝ?/
ግእዝ ቋንቋ ኢትዮጵያዊ ቋንቋችን ነው፡፡ በራሱ ዜጎች አማካኝነት በራሱ ፊደል የተቀመረ ኢትዮጵያዊ ቋንቋ ነው፡፡ ግእዝ የማን ቋንቋ/የማን ወገን/ ነው ብለን ስንጠይቅ በስድስት ክፍሎች ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡ እነርሱም፡-
፩. የእግዚአብሔር፣ የመላእክትና የአዳም ቋንቋ ነው የሚሉ
ባጠቃላይ እነዚህ ሊቃውንት ከማስረጃነት ከማያቀርቡት መካከል፡-
W የእግዚአብሔር ቋንቋ ለማለታቸው ንግበር ሰብዓ በአርያነ ወበአምሳሊነ ዘፍ.፩ በሚለው ላይ ንግበር የሚለው ቃል የግእዝ ግስ ርባታ ሣልሳይ አንቀጽ መሆኑ፤
W የመላእክት ቋንቋ ለማለታቸው «ንቁም በባህላዌነ እስከ ንረክቦ ለአምላክነ» በሚለው ላይ ንቁም የሚለው ቃል የግእዝ ግስ ርባታ ሣልሳይ አንቀጽ መሆኑ፤
W የአዳም ቋንቋ ለማለታቸውም አዳም ከተሰጠው ኃብታት መካከል አንዱ የግእዝ ቋንቋ ነው በግእዝ ቋንቋም ይጸልይበት ነበር፡፡  አዳም ጥፋትን ባጠፋ ጊዜ ግን ከተነሳው ጸጋ መካከል አንዱ የግእዝ ቋንቋን ነው በአቤል ፋንታ ለተወለደው ለሴት እግዚአብሔር ፊደላትን ገለጸለት የሴት ልጅ ሔኖስም በቃሉ አጠናቸው ሆኖም ግን የአዳም ልጆች ጸጋ ዕውቀትን ስለተነሣቸው ረሱት፡፡ ዳግመኛም ለአዳም ትውልድ ለሔኖክ እግዚአብሔር በጸፍጸፈ ሰማይ/በሰማይ ጣርያ/ ፊደላትን አሳየው ሔኖክም ብልህ ነበርና በሸክላ ጻፈው፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ ክፍልም በቀደምትነት የመጀመሪያ የሆነውን መጽሐፈ ሔኖክን በ፬ሺህ፲፬ ቅ.ል.ክ ጻፈበት ይኸም እስከ ቅድመ ስናዖር ድረስ ቆየ፡፡ ከዚህም በኋላ የዓለም ቋንቋ ዓይነት ቋንቋዎች ተደበላለቀ በኖኅ ጊዜም ኖኅ ለ፫ቱ ልጆቹ ለሴም ለካምና ለያፌት ቦታንና ቋንቋን አወረሰ፡፡
Ä ይህንንም ሐሳብ ከሚደግፉት ምሁራን መካከል፡
Rአለቃ አስረስ የኔሰው «የኢትዮጵያ ፊደሎች የአዳምና የመላእክት መነጋገሪያ ነበሩ» ብለዋል፡፡ 



R አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ «ግእዝ የመጀመሪያ የሰው ልጀ ቋንቋ ነው የተሰጠውም ከእግዘአብሔር ነው፡» ይላሉ፡፡  ለዚህም፡-    
          ‹‹ከንጉሡም ከእግዜር ከባለቤቷ
              ስለተሰጠች እቴጌነቷ
              እንዲህ ብታይዋት ደሃ መስላችሁ                        
              ባለጸጋ ናት ግእዝ ቋንቋችሁ፡፡›› ብለዋል፡፡
R ክንፈ ርግብ አታለል «ግእዝ ማለት አንደኛ መጀመሪያ ማለት ነው» በማለት ከቃሉ ፍቺ በመነሳት የቋንቋውን አዳማዊነት አስረግጠዋል፡፡ ለዚህም ሁለት የውጭ ሀገር ምሁራንን ጠቅሰዋል፡፡ «...  ይህን መሠረት በማድረግ ሲዲ ጳውሎስና መአልም ዮሐንስ የተባሉ ሁለት ጀርመናውያን ሊቃውንት ልሳነ ግእዝ የአዳም ቋንቋ ነው ብለውታል፡፡» ይላሉ፡፡
R/ ኢሳይያስ ዓለሜ እንግዳዊ ቀደም ሲል «ግእዝ ከእግዚአብሔር ስለመውረዱ አብደልመጅድ አቢድን የተባለ ዐረብ በካይሮ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቋንቋ መምህር በዳነአል- ሐበሻ -ውእል- ዐረብ፤ በሐበሻና በዐረቦች መካከል በሚል መጽሐፉ ግእዝ ከሰማይ የወረደ ቋንቋ በማለት ጽፏል» ብለው ገልጸዋል፡፡
፪. የካም ቋንቋ የሚሉ፡-
ግእዝን የደቡብ ሴማዊ ልሳን ሳይሆን በዐረብ ምድር የመጀመሪያዎቹ የአፍሪካውያን ወይም የኩሻውያን /የካም/ ቋንቋ ነው የሚሉ ናቸው ከነዚህም መካከል፡-
® ኤቢ ዶጐፖልስኪ /A.B Dogopolsky/ እና ኢጎር ዲያክኖፍት /Igor Diaknoft/ - ከሶቭየት ምሁራን፡፡
® ቸክ አንታ ዲዮፕ /Cheek Anta Diop /
® አቤንጃ
® ሺናይዳር
® አለቃ አስረስ የኔሰው
® መሪጌታ ልሳነ ወርቅ ገብረ ጊዮርጊስ
® ኃይሉ ኃብቱ
® አየለ በከሪ ወዘተ ናቸው
በተለይም ከላይ ካየናቸው ምሁራን መካከል የግእዝና የአቡሻክር ሊቅ የሆኑት አለቃ አስረስ የኔሰው «ግዕዝን ካም ወደ አፍሪካ ይዞት የመጣ ኖኅ በሕይወቱ ዓለምን ልጆቹ ለሴም ለካም ለያፌት ባካፈለ ጊዜ ስለ ዓለም መከፋፈል ነው፡፡» ኩፋ.፱ .ዘፍ.፪ ሲሉ፤ መሪጌታ ልሳነወርቅም «እኛ የኢትዮጵያውያን ሕዝብ ከግዕዝ ቋንቋችን በላይ እሊህ ሕጸጽ የሌለባቸው የተሟሉ ፳፮ ፊደሎችን



የወረስናቸው ከአባታችን ካም በ፪ሺሕ ፯፻፯ ዓመተ ዓለም ሲሆን፤ የሴም ዘር የሆኑ ሕዝብ የወረሱት አበገደ ብሎ እስከ ያሉትን ፳፪ቱን ፊደሎች ስለሆነ ከዚያ ዘሩን እያበዙ መጻሕፍታቸውን ይጽፋሉ፡፡» ብለዋል፡፡
 ፫. የሴም ቋንቋ የሚሉ
£ ሲዲ ጳውሎስ
£ መርቶኒን እና ሊኦኔል ቤንደር ከኢትዮጵያ የወጣ ቋንቋ ነው የሚል አቋምም አላቸው፡፡
£ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ
£/ ጌታቸው ኃይሌ፡- የግእዝ ተናጋሪዎች እነማን እንደነበሩ ግን አላውቅም የሚሉ ከላይ ካየናቸውም መካከል አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ የግእዝን፣ የሱርስትን፣ የዐረብን እና የዕብራይስጥ ቋንቋን ሴማዊ የሚሉ ናቸው፡፡
] በአንጻሩ ካም ወይም ሴም የሚለውን ቃል ከቋንቋ ጋር በማገናኘት የተጠቀመበት የጀርመን መልእክተኛ ጆህን ሉድዊግስፍ /Johunn Lvowiskapf/ ነው፡፡ ካርል ፍሬድሪክ ሌፐሲየስ /Karl Friedrich Lepsius/ ደግሞ ካምም ሴማዊም አይደለም የሚለው ከግብጻውያን ቋንቋ ጥናት በመነሣት ከቋንቋ ሰዋሰው ውስጥ የጾታ ሥርዓትን በማየት ነው፡፡
፬. የግእዝ ቋንቋ ከሌሎች ቋንቋዎች ጋር በማነጻጸር አስተያየት ከሰጡት መካከል
­ ደራሲ ማሞ ውድነህ ቋንቋውን ጥንታውያት ከሆኑት የግሪክና የላቲን ቋንቋዎች ጋር በማነጻጸር እንዲህ ይላሉ፡፡ ጥንታዊው የግእዝ ቋንቋ እጅግ የተጣራ በመሆኑ ለግሪክና ለላቲን ቋንቋ ተወዳዳሪ ለመሆን ይቃጣዋል፡፡ ይበሉ አንጂ በቀሪው ጽሑፋቸው ስለ ቋንቋው ጥንታዊነት በሰፊው አትተዋል፡፡
­ አባ ተከስተ /መድኅን የግእዝን ቋንቋ ከሀገር ውስጥ ቋንቋዎች ጋር በማነጻጸር በግንባር ቀደምትነት በማሰለፍ እንዲህ ይላሉ «አማርኛም ሆነ ትግርኛ እንዲሁም ሌሎች የአሁኑ ቋንቋዎቻችን ረጅም እድሜ እንደሌላቸው ግልጽ ነው፡፡  ... ኢትዮጵያ ከሠለጠኑ የድሮ ሕዝብ ውስጥ የሚያስቁጥራት አንደኛው ሀብቷ ... ጥንታዊው ቋንቋዋ ግእዝ ነው» ይላሉ፡፡  


፭.  ከተናጋሪዎች ሕዝቦች/ጎሳዎች/ ጋር በማያያዝ አስተያየታቸውን ከሰጡት መካከል፡-
n አባ /ኢየሱስ ኃይሉ ግእዝ ግእዛውያን አግአዝያን ወደ ብሔረ አግአዚ የተሻገሩበት የመጡበትም ሐበሻት የተባሉ አንድ የዓረብ ዘር ሰሐርታን ከተባለ ከባሕር ጠረፍ የሚገኝ ከየመን አውራጃ ተነሥተው ወደ ኢትዮጵያ ገብተው ነበር፡፡ ...ከተባለው ዘመን ፊት ግእዝ ወደ ኢትዮጵያ ደረሰ ለአገሩ የሚሆን ቋንቋ ይዘውም ገቡ፡፡ መምጣታቸው ሳባ ከሚባል ደቡባዊ ዐረብ አውራጃ ነው የመጡትንም ቋንቋ እንደ ባሕርያዊ አካሄድ ከአገሩ ቋንቋ ጋር በትንሽ ተስማምቶ ተቀላቅሎ ግእዝን ወለደ፡፡
፮. አፍሮ እስያዊ ነው የሚሉ
በአሁኑ ሰዓት ያለው የሥነ ልሳን ጥናት /Philology/ ከሐረገ ዘር(የካም፣ የሴም) ከማለት ይልቅ መልክዐ ምድራዊ በመኾኑ የካም የሴም ቋንቋ መባሉ ቀርቶ በአጠቃላይ በአፍሮ እስያነት ውስጥ ነው መድቦ የሚየየው ይህንንም ሐሳብ ከሚደግፉት መካከል፡-
t / ባየ ይማም
t ዮሴፍ ግሪን በርግ /Joseph Green berg/
t / ደሴ ቀለብ 

]]] ማጠቃለያ፡- የዚህ ጽሑፍ አዘጋጆችም ባጭሩ ግእዝ ኢትዮጵያዊው ቋንቋችን ጥንታዊ ነው፡፡በራሱ ዜጎች አማካይኝነት በራሱ ፊደል የተቀመረም ነው፡፡ አፍሪካዊ የኢትዮጵያ ልሳንም ነው ይላሉ፡፡