Saturday, April 27, 2013

እግዚአብሔር በወዴት ይገኛል ቢሉ

† በደዌ ደኛ በአልጋ ቁራኛ ተይዘዉ በሚማቅቁ፣አስታማሚና ጠያቂ አጥተዉ ዕለተ ሞታቸዉን በሚናፍቁ ምስኪን ህሙማን መካከል እግዚአብሔር ይገኛል፡፡
† የፍርቱና ጉዳይ ሆኖባቸዉ በባዶዉ አስፋልት ላይ ካርቶን አንጥፈዉ በሚተኙ ዝናቡ፣ ቁሩ፣ ዋዕዩ በሚፈራረቅባቸዉ፣ቆሻሻ ገንዳ ላይ ተንጠላጥለዉ የበሰበሰ ፍራፍሬን ቀለባቸዉ ባደረጉ፣ችጋር ጠንቶባቸዉ መማሪያ ክፍል ዉስጥ እንዳሉ በረሀብ በሚያሸልቡ የድሀ ድሀ ልጆች መካከል እግዚአብሔር ይገኛል፡፡
† በግፈኞች ፍትህ ተንጋዶባቸዉ ባልዋሉበት እንደዋሉ፣ባልሰሩት እንደሰሩ ተደርገዉ በጨለማ እስር ቤት በተወረወሩ፣ብረት በተቆለፈባቸዉ የህሊና ታሳሪዎችና የህዝብ ጠበቆች መካከል እግዚአብሔር ይገኛል፡፡
† በእኩይ ባሎቻቸዉ አካላዊም ሆነ ስነ ልቦናዊም ጥቃት በደረሰባቸዉ፣እጅግ የከበደዉን መከራ መቋቋም ተስኗቸዉ ቀኑ በጨለመባቸዉ እንዲሁም ቢጮሁ ቢጮሁ ሰሚ አጥተዉ ሌት ተቀን በሰቆቃ በሚባዝኑ አንስቶች መካከል እግዚአብሔር ይገኛል፡፡
† ለዚህች ሀገር የሚችሉትን ሁሉ አበርክተዉ አቅማቸዉ ሲደክም ጉልበታቸዉ ሲከዳ ጧሪ ቀባሪ ጧሪ ቀባሪ በማጣት ቤታቸዉ በፈረሰባቸዉ እንዲሁም ለልመና እጅ በሰጡ አዛዉንት አባቶችና አሮጊት እናቶች መካከል እግዚአብሔር ይገኛል፡፡ 
ታዲያ እነዚህን አካላት ሲራቡ በማብላት፣ሲጠሙ በማጠጣት፣ ሲታሰሩ በመጠየቅ፣ሲታረዙ በማልበስ፣ሲያዝኑ በማጽናናት ሲታመሙ በመንከባከብ በመርዳት ከጎናቸዉ ሆነን ችግራቸዉን ከተካፈልን ከእግዚአብሔር ጋር እንገናኛለን ምክንያቱም የእርሱ ቦታዉ እዚህ ነዉና ሁሌም በፍቅሩ ይጎበኘናል እኛ አናየዉ ይሆናል እንጂ እርሱ ይመለከተናል መሻታችንን ሁሉ ይፈጽምልናል የሚበልጠዉንም ያደርግልናል፡፡ኦ! ጌታ ሆይ ከአንተ ጋር መሆን እንዴት መባረክ ነዉ፡፡

Monday, April 15, 2013

ኒቆዲሞስ


ኒቆዲሞስ ዮሃ ፫፤፪
                 ከፈሪሳዊያን ወገን የሆነ የአይሁድ አለቃ የሆነ ኒቆዲሞስ የሚባል አንድ ሰው በሌሊት ወደ ጌታ እየሄደ ይማር ነበር ኒቆዲሞስ ከቀኑ ክፍለ ጊዜ ይልቅ የሌሊቱን ጊዜ ለትምህርት ለምን መረጠ ?
                     ፩. ኒቆዲሞስ መምህር ስለነበር ስማር ሰዎች ቢያዩኝ ውዳሴ ከንቱ መምህር መባል ይቀርብኛል ብሎ ነው እኛስ ዛሬ የዘላለም ህይወት የሚሰጠንን ቅዱስ ቃል ብትህትና መማር ሲገባን ለምድራዊ ክብር ብለን በቀን ጊዜያችን መማር ያልቻልን ስንቶቻችን ነን ስለዚህ ቀን ጊዜአችንን በአግባቡ ልንጠቀምበት ይገባል
 ‹ ማንም ሊሰራ የማይችልባት ሌሊት ትመጣለችና › ዮሃ ፱፤፬
 ፪.ኒቆዲሞስ የአይሁድ መምህር ስለነበር እንዳያዩት ፈርቶ ሌሊት እየመጣ ይማር ነበር እኛስ ዛሬ ልባችን የተረዳውን እውነት በግልጥ እንዳንፈጽም በፍራቻ በይሉኝታ የምንሰውር ስንቶቻችን ነን
 ‹ፍጹምፍቅር ፍርሃት የለውም ፍርሃት ቅጣት አለውና› ፩ዮሃ ፬፤፲፰   ፍርሃትን አስወግደን ለእውነት ልንቆም ይገባል
     ፫ ኒቆዲሞስ ከቀን ልብ ይልቅ የሌሊት ልብ የተካተተ ስለሆነ በሙሉ ልቡ በማስተዋል ለመማር ስለፈለገ ከቀኑ ክፍለ ጊዜ ይልቅ የማታውን መረጠ ዛሬስ ስንቶቻችን ነን ቅዱስ ቃሉን በማስተዋል ከልብ ሆነን የምንማር የሰማነው ቅዱስ ቃል በህይወታችን ፍሬ እንዲያፈራ ቅዱስ ቃሉን ከልብ ሆነን በማስተዋል ልንሰማ ይገባናል ቃሉን ሰምቶ የሚያስተውል ልብ መልካም መሬት ተብⶀል
‹ በመልካም መሬት የተዘራውም ይህ ቃሉን ሰምቶ የሚያስተውል ነው› ማቴ ፲፫፡፳፫
    አንዳንዶቻችን ጸሎት እያደረግን እንኳን አንደበታችን የእግዚአብሄርን ቃል ይነዳል ልባችን ሌላ ቦታ ይንጎዳጎዳል በማህበር ጸሎትም አብረን እየጸልይን በመሃል ሳይን አውት አርገን ልክ ሲፈጸም አለቀ እንዴ ብለን ሳይን ኢን የምናደርግ አንጠፋም
            ፬ ሌሊት ጨለማ ነው ብርሃን የለም ይህም የኃጢአት ምሳሌ ነው ኒቆዲሞስ በሌሊት መምጣቱ በኃጢአት እንዳለ ንስሃ እንደሚፈግ ያስረዳናል ዛሬስ ስንቶቻችን ነን ቅዱስ ቃሉን ስንሰማ በተአምኖ ኃጢአት በንስሃ ውስጥ ሆነን የምንሰማ ያለንስሃ የምንሰማው ቃል በህይወታችን ፍሬ የማፍራት እድሉ ጠባብ ነው ምክንያቱም በንስሃ ከልባችን ያልጸዱት ክፉ ምኞቶች እንደ እሾህ ሆነው ያንቁታልና
‹ሌላውም በእሾህ መካከል ወደቀ እሾህም ወጣና አነቀው› ማቴ፲፫፤፰  ተብሎ የተጻፈው ለዚህ ነው
            ፭ ሌሊት የቆየው ኪዳን ወይም የብሉይ ኪዳን ምሳሌ ነው ኒቆዲሞስም እኔ ምሁረ ኦሪት እንጂ ምሁረ ወንጌል አይደለሁም ወንጌልን ካንተ እማር ዘንድ ያስፈልገኛል ሲል በሌሊት ይመጣ ነበር ብሉያት ከሓዲሳት ጋር ተዋህደው ሲተረጎሙ ሰሙና ወርቁ ተጣምሮ የሕይወት ትምህርት ያስገኛል አንዳንዶች ዛሬ ብሉያት ጭራሽ አያስፈልጉም ሲሉ ይደመጣሉ ነገር ግን እንደ ኒቆዲሞስ ሁለቱን ኪዳናት አዋህዶ መጓዝ ትክክለኛው መንገድ ነው ለዚህም ነው ጌታ ሲያስተምር‹እውነት እላችኋለው ሰማይና ምድረስኪያልፍ ድረስ ከህግ አንዲት የውጣ ወይም አንዲት ነጥብ አታልፍም› ማቴ፭፤፲፰ በማለት አበክሮ የተናገረው ኒቆዲሞስ ምንም እንኳን የቀኑ ክፍለ ጊዜ ባይመቸውም በሌሊቱ ሰአት ለመማር ችⶀል እኛም ከሱ ተምረን ከልብ ካለቀሱ እንባ አይጠፋምና ምንም ስራ ቢበዛብን ለቅዱስ ቃሉ ጊዜ አይጠፋምና ህይወት ለሚገኝበት ትምህርት ጊዜ ልንሰት ይገባል።

የዐቢይ ጾም ስድስተኛ ሰንበት ገብር ሔር

ምንጭ፦ አትሮንስ - የዲያቆን ኤርምያስ ነቢዩ ገጽ
የዐቢይ ጾም ስድስተኛ ሰንበት ገብር ሔር (ቸር አገልጋይ) የተሰኘው ሲሆን ይህንን ስያሜ ያገኘበትም ምክንያት ከዋዜማው ጀምሮ የሚዘመረው ጾመ ድጓ ‹‹ገብር ሔር ወገብር ምእመን ገብር ዘአስመሮ ለእግዚኡ፤ ጌታውን ያስደሰተው አገልጋይ ታማኝና ቸር አገልጋይ ነው፡፡  ገብርሔር በጎ አገልጋይ ማለት ሲሆን የስያሜውን መነሻ የምናገኘው በዕለቱ ሥርዓተ ቅዳሴ ከሚነበበው የወንጌል ክፍል ማቴ.25-14-30 ነው፡፡

ምስባክ     መዝ. 39÷8 
"ከመ እንግር ፈቃደከ መከርኩ አምላኪየ፡፡ 
ወሕግከኒ በማዕከለ ከርሥየ፡፡
 ዜኖኩ ጽድቀከ በማኅበር ዐቢይ፡፡"

ትርጉም፦ አምላኬ ሆይ፥ ፈቃድህን ለማድረግ መከርሁ፥
 ሕግህም በልቤ ውስጥ ነው።
 በታላቅ ጉባኤ ጽድቅህን አወራሁ።

ወንጌል
ማቴ. 25÷14-30 “መንገድ እንደሚሄድ÷ አገልጋዮቹንም ጠርቶ ሊያተርፉበት ገንዘቡን እንደ ሰጣቸው ሰው እንዲሁ ይሆናልና፤ ለእያንዳንዱ እንደ ችሎታው ለአንዱ አምስት÷ ለአንዱ ሁለት÷ ለአንዱም አንድ ሰጠና ወዲያውኑ ሄደ፡፡ ያ አምስት መክሊት የተቀበለውም ሄደ፤ ነግዶም ሌላ አምስት መክሊት አተረፈ፡፡ እንዲሁም ሁለት የተቀበለው ሌላ ሁለት አተረፈ፡፡ አንድ መክሊት የተቀበለው ግን ሄዶ ምድርን ቈፈረና የጌታዉን ወርቅ ቀበረ፡፡ ከብዙ ጊዜም በኋላ የእነዚያ አገልጋዮች ጌታ ተመልሶ ተቈጣጠራቸው፡፡ አምስት መክሊት የተቀበለውም ቀረበና፡- አቤቱ አምስት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር፤ እነሆ ሌላ አምስት አተረፍሁ ብሎ አምስት መክሊት አስረከበ፡፡ ጌታውም፡- መልካም÷ አንተ የታመንህ በጎ አገልጋይ በጥቂት የታመንህ ስለ ሆንህ በብዙ እሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው፡፡ ሁለት መክሊት የተቀበለውም መጥቶ፡- አቤቱ÷ ሁለት መክሊትን ሰጥተኸኝ አልነበረምን? እነሆ ሌላ ሁለት መክሊትን አተረፈሁ አለ፡፡ ጌታውም፡- መልካም÷ አንተ የታመንህ በጎ አገልጋይ በጥቂቱ የታመንህ ስለ ሆንህ በብዙ አሾምሃለሁ፤ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ አለው፡፡ አንድ መክሊት የተቀበለውም መጣና እንዲህ አለ፡- አቤቱ÷ አንተ ካልዘራህበት የምታጭድ÷ ካልበተንህበትም የምትሰበስብ ጨካኝ ሰው እንደ ሆንህ አውቃለሁ፤ ስለ ፈራሁም ሄድሁና መክሊትህን በምድር ውስጥ ቀበርሁ፤ እንግዲህ እነሆ÷ መክሊትህ፡፡ ጌታውም መልሶ አለው፡- አንተ ክፉና ሰነፍ አገልጋይ÷ እኔ ካልዘራሁበት የማጭድ÷ ካልበተንሁበትም የምሰበስብ ጨካኝ ሰው እንደ ሆንሁ ታውቃለህን? ገንዘቤን ለለዋጮች መስጠት በተገባህ ነበር፤ እኔም ራሴ መጥቼ ገንዘቤን ከትርፉ ጋር በወሰድሁ ነበር፡፡
 ከዚያ የቆሙትንም እንዲህ አላቸው፤ ይህን መክሊት ከእርሱ ተቀብላችሁ ዐሥር መክሊት ላለው ስጡት፡፡ ላለው ሁሉ ይሰጡታልና፤ ይጨምሩለታልም፤ ለሌለው ግን ያንኑ ያለውን ይወስዱበታል፡፡ ክፉውን አገልጋይ ግን÷ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት በውጭ ወደ አለ ጨለማ አውጡት፡፡


ዲያቆን (ምንባብ) 
2ኛ ጢሞ.2÷1-15 ልጄ ሆይ÷ አንተም በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ በርታ፡፡ በብዙ ምስክሮች ፊት ከእኔ የሰማኸውን ትምህርት ለሌሎች ሊያስተምሩ ለሚችሉ ለታመኑ ሰዎች እርሱን አስተምራቸው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስን እንደሚያገለግል በጎ አርበኛ ሆነህ መከራ ተቀበል፡፡ ወደ ሰልፍ የሚሄድ÷ አለቃውን ደስ ያሰኝ ዘንድ ነው እንጂ የዚህን ዓለም ኑሮ አያስብምና፡፡ የሚታገልም ቢሆን እንደ ሕጉ ካልታገለ አክሊልን አያገኝም፡፡ የሚደክም አራሽም አስቀድሞ ፍሬውን ሊያገኝ ግድ ነው፡፡ ያልሁህን አስተውል፤ እግዚአብሔርም በሁሉ ነገር ጥበብን ይስጥህ፡፡
 በወንጌል እንደምሰብከው÷ ከሙታን ተለይቶ የተነሣውን ከዳዊት ዘር የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን አስበው፡፡ ስለ እርሱም እንደ ወንጀለኛ አስክታሰር ድረስ መከራ እቀበላለሁ፤ የእግዚአብሔር ቃል ግን አይታሰርም፡፡ ስለዚህ እነርሱ ደግሞ በኢየሱስ ክርስቶስ ያለውን ሕይወትና የዘለዓለም ክብር በሰማያት ያገኙ ዘንድ÷ ስለ ተመረጡት ሰዎች በሁሉ ነገር እታገሣለሁ፡፡ ነገሩ እውነት ነው፤ ከእርሱ ጋር ከሞትን ከእርሱ ጋር ደግሞ በሕይወት እንኖራለን፡፡ ብንታገሥም ከእርሱ ጋር ደግሞ እንነግሣለን፤ ብንክደው ግን እርሱም ይክደናል፡፡ ባናምነውም እርሱ የታመነ ሆኖ ይኖራል፤ ራሱን መካድ አይቻለውምና፡፡
እንግዲህ ይህን አሳስባቸው፤ በቃልም እንዳይጣሉ÷ በእግዚአብሔር ፊት ምከራቸው፤ ይህ ምንም የማይጠቅም÷ የሚሰሙትንም የሚያፈርስ ነውና፡፡የእግዚአብሔርን ቃል በእውነት አቃንቶ ሲያስተምር እንደማያፍር ሰራተኛ ሆነህ ፣ራስህን የተመረጠ አድርገህ  ለእግዚአብሔር ታቀርብ ዘንድ ትጋ።  

ንፍቅ ዲያቆን (ምንባብ)

 1ኛ ጴጥ.5÷1-11 እንግዲህ እኔ ከእነርሱ ጋር ሽማግሌ÷ የክርስቶስም መከራ ምስክር÷ ደግሞም ሊገለጥ ካለው ክብር ተካፋይ የሆንሁ በመካከላቸው ያሉትን ሽማግለዎችን እማልዳቸዋለሁ፡፡ በእናንተ ዘንድ ያሉትን የእግዚአብሔርን መንጋዎች ጠብቁ፤ ስትጠብቁአቸውም እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ በውድ እንጂ በግድ አይሁን፤ በበጎ ፈቃድ እንጂ መጥፎውን ረብ በመመኘትም አይሁን፡፡ ለመንጋዉ ምሳሌ ሁኑ እንጂ ሕዝቡን በኀይል አትግዙ፡፡ የእረኞችም አለቃ በተገለጠ ጊዜ የማይጠፋውን የክብር አክሊል ትቀበላላችሁ፡፡ እንዲሁ እናንተ ጐልማሶች ሆይ÷ ለሽማግሌዎች ተገዙ፤ ሁላችሁም ትሕትናን ልበሷት፤ እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ያዋርዳልና፤ ራሳቸውን ዝቅ የሚያደርጉትን ግን ያከብራቸዋል፡፡
እንግዲህ በጐበኛችሁ ጊዜ ከፍ ከፍ ያደርጋችሁ ዘንድ ከጸናችው ከእግዚአብሔር ክንድ በታች ራሳችሁን አዋርዱ፡፡ እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት፡፡ እንግዲህ ዐዋቂዎች ሁኑ፤ ትጉም፤ ጠላታችሁ ጋኔን የሚውጠውን ፈልጎ÷ እንደሚያገሳ አንበሳ ይዞራልና፡፡ እርሱንም በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት፤ እንዲህም ያለ መከራ በዓለም በአሉ ወንድሞቻችሁ ሁሉ እንደሚፈጸም ዕወቁ፤ ፍቅርንም አጽንታችሁ ያዙአት፡፡ በኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ዘለዓለም ክብሩ የጠራችሁ የጸጋ ሁሉ አምላክ ለጥቂት ጊዜ መከራን ከተቀበላችሁ በኋላ ፍጹማን ያደርጋችኋል፤ ያጸናችኋል፤ ልባሞችም ያደርጋችኋል፡፡ለእርሱ ክብርና ኅይል እስከ ዘለአለም ይሁን፤አሜን።
ንፍቅ ቄስ (ምንባብ)
የሐዋ.1÷6-8 እነርሱም ተሰብስበው ሳሉ÷ "ጌታ ሆይ÷ በዚህ ወራት ለእስራኤል ልጆች መንግሥትን ትመልሳለህን?” ብለው ጠየቁት፡፡ እርሱም መልሶ እንዲህ አላቸው÷ “አብ በገዛ ሥልጣኑ የወሰነውን ቀኑንና ዘመኑን ልታውቁ አልተፈቀደላችሁም፡፡ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኅይልን ትቀበላላችሁ፤በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ሁሉ፣በሰማሪያና እስከ ምድር ዳርቻ ድረስም ምስክሮቸ ትሆኑኛላችሁ።"

ቅዳሴ
ዘባስልዮስ

Sunday, April 14, 2013

ታማኝነት


ታማኝነት ማለት ምሎ የማይከዳ፤አደራ የማያጠፋ፤የያዘዉን በቀላሉ የማይለቅ፤የማያወላዉል፤ለምስክርነት የሚበቃ ማለት ነዉ፡፡ታማኝ ሰዉ የሚያምነዉንና መልካም ነዉ የሚለዉን ይናገራል የሚናገረዉንም ይሠራል፡፡ባሠማሩትም ሥራ ላይ በሚቻለዉ ሁሉ እንከን ሳያስገባ ጠብቆ ይገኛል፡፡በኃላፊነት ቦታ ቢያስቀምጡት ያለምንም አድሎዎና ወገናዊነት ያስተዳድራል፡፡
አንዳንድ ሰዎች ግን ታማኝነትን እንደቀላል ነገር ስለሚመለከቱት እምበዛም ትኩረትአይሰጡትም፡፡ስለዚህም በሥራቸዉ፤በትዳራቸዉ፤በ አጠቃላይ ኑሯቸዉ ወዘተ…ታማኝ ለመሆን አይጥሩም፡፡ነገር ግን ታማኝነት ከሰዉና ከእግዚአብሔር ጋር የምንገናኝበትና ማንነታችን(ክርስቲያናዊ ሕይወታችን)የሚለካበት ሚዛን ነዉ፡፡በመሆኑም አንድ ክርስቲያን በኑሮዉ ሁሉ በሚከተሉት ነገሮች ታማኝነቱን ሊገልጥ ይገባዋል፡፡
 


ለራስ ታማኝ መሆን

ለራሳቸዉ ታማኝ ያልሆኑ ሰዎች በተናገሩት አይጸኑም፡፡እንደ ዉኃ ላይ ኩበት ሁል ጊዜ ወዲያና ወዲህ እንደዋለሉ ይኖራሉ፡፡ለጊዜዉ የሚያገኗቸዉን ጥቅሞች በማሰብና በአካባቢያቸዉም ተፅዕኖ ምክንያት በዉሳኔአቸዉ አይረጉም፡፡ስለዚህ‹‹አደርጋለሁ››ብለዉ የሚወስኑትና የሚያደርጉት አይገናኝም፡፡የሚያስፈልጋቸዉንና የማያስፈልጋቸዉን ለመለየት ይቸግራሉ፡፡ሌሎችንም ለማመን ስለሚከብዳቸዉ ሕይወታቸዉ በጥርጥር የተመላ ይሆናል፡፡ስለዚህ ክርስቲያን ለሌሎች ከመታመኑ በፊት በቅድሚያ ለራሱ ሊታመን ይገባዋል፡፡ሁል ጊዜም የሌሎችን ይሉኝታ እያሰበ ብቻ ሳይሆን እዉነትን ይዞ መጓዝ ይኖርበታል፡፡እንደዚያ ከሆነ በተናገረዉ ይጸናል፤አይዋሽም፤ለጊዚያዊ ጥቅም ራሱን አሳልፎ አይሰጥም፡፡
 

ለእግዚአብሔር ታማኝ በመሆን

እግዚአብሔር ለቅዱሳን የገባዉን ቃል ኪዳን የሚያከብርና የሚፈጽም በቃሉ የታመነ ነዉ፡፡እንደዚሁም የእርሱ የሆኑ ሁሉ ታማኝ እንዲሆን ይፈልጋል፡፡በመሆኑም ክርስቲያኖች የክርስቶስ ሙሽሮች ነንና በፍጹም ፍቅር ለእርሱ ልንታመን ይገባናል፡፡ልባችንና አጠቃላይ ሰዉነታችንን ለእግዚአብሔር ፍቅር አሳልፈን ከሰጠን ከሁሉም በላይ ለእርሱ ያለንን ፍቅር ስለምናስቀድም ለመታመን አንቸገርም፡፡ቃሉን ለማክበርና ትዕዛዙን ለመፈጸም እስከመጨረሻዉም በቤቱ ለመጽናት እንችላለን፡፡ቅዱስ ዮሴፍ በግብጽ በስደት ሲኖር የጲጥፋራ ሚስት ኃጢያጥ እንዲፈጽም ትገፋፋዉ ነበር፡፡ተመልካች ሰዉ በሌለበት ሰዓት ስታስጨንቀዉ‹‹እንዴት በ እግዚአብሔር ፊት ኃጢያትን እሰራለሁ?››በማለት ለፈጣሪዉ ያለዉን ፍቅርና ታማኝነት በቃሉ ብቻ ሳይሆን በተግባርም ገለጸ፡፡ዘፍ 39-9፡፡ዮሴፍ በዚህን ጊዜ ኃጢያትን እንቢ በማለቱ የሚደርስበት ስቃይ አልታየዉም ከሁሉም በላይ የሆነዉና በስደትም ያልተለየዉ የ እግዚአብሔር ፍቅር እንጅ!በዘመናችን ግን ብዙ ሰዎች የሚገዙት መግባት መዉጣታቸዉን ለሚቆጣጠረዉና ለአፍታ እንኳን ለማይለያቸዉ ለእግዚአብሔር ሳይሆን ለሰዎች ነዉ፡፡ስለዚህም ብዙ ወንጀሎችና ኃጥያቶች የሚፈጸሙት ሰዎች አያዩኝም ተብሎ በሚታሰብባቸዉ በጨለማ ጊዜያት ነዉ፡፡ፈሪሃ እግዚአብሔር ሳይኖራቸዉና ፍቅሩ ሳያስገድዳቸዉ በአካባቢአቸዉ ያሉትን ሰዎች ብቻ በመፍራት የሚኖሩ ሰዎች ብዙዉን ጊዜ ተደብቀዉ ይበድላሉ፤ይዋሻሉ፤ጉቦ ይሰጣሉ፤ይቀበላሉ፤ አደራ ያጎድላሉ ወዘተ…….ስለዚህ ክርስቲያን የሚሰራዉን ሁሉ ለእግዚአብሔር ፍቅር ብሎ ፈሪሃ እግዚአብሔር ኖሮት ከሠራ በተሰማራበት ሁሉ ታማኝነት የ እግዚአብሔር ፍቅር መለኪያና ለታላቅ ክብሮትም የሚያበቃ ነዉ፡፡ መዝ 36-4 ሮሜ 8-35
 

ለሎች ሰዎች ታማኝ በመሆን

ክርስቲያን በመቅረዝ ላይ ያለ መብራት ነዉና ለራሱ ብቻ አይኖርም፡፡ብርሃኑን ለሌሎች ያበራል፡፡ስለዚህ በዕለት ለዕለት ኑሮዉ ከሰዎች ጋር ስለሚገናኝ በተሰማራበት ሁሉ ታማኝ ሊሆን ያስፈልጋል፡፡በተለይም እዉነተኛ ፍቅር በልቡ ያለዉና ሌሎችን እንደራሱ አድርጎ ለሚወድ ሰዉ ታማኝነት ምግባሩ ነዉ፡፡አደራ ቢቀበል አይክድም፤የራሱን ጥቅም አስቀድሞ አይዋሽም፤በሀሰት አይመሰክርም፤የገባዉን ቃል ኪዳን አያፈርስም፡፡ለሌሎች ታማኝ መሆን የሚጀምረዉ ከአነስተኛና እኛ ቀላላ አድርገን ከምንገምተው ነገር በመነሳት ነዉ፡፡የተሰጠችን አነስተኛ አደራ በመጠበቅ ምስጢር መያዝ ወዘተ..እንደዚህ በጥቂቱ የታመነ በብዙ ይሾማል ማቴ25-21 ሌላዉ የዘመናችን ችግር የብዙ ሰዎች በትዳራቸዉ ታምኖ አለመገኝት ነዉ፡፡ትዳር ያልመሰረቱ ወጣቶች እነረኳን(ለምን ትዳር አትመሰርትም?አትመሰርችም?)ተብለዉ ሲጠየቁ‹‹የሚታመን ሰዉ አለ ብላችሁ ነዉ?››ይሆናል መልሳቸዉ፡፡በትዳር ላይ ያለዉ ዉስልትና አለመተማመን ጋብቻን ያህል በብዙዎች ዘንድ የሚያስመርር አድርጎታል፡፡ሌላዉ ችግር ደግሞ በተሰማሩበት ወይም በተሾሙበት የስራ መስክ ታማን ሆኖ አለመገኝት ነዉ፡፡ምዝበራ፤ጉቦኝነትና አድልዎ በ የጊዜዉ የሚሰሙና ብዙ ሰዎች የሚዎድቁበት ጉዳይ ነዉ፡፡እንግዲህ አንድ ክርሰቲያን ታማኝ መሆን አለበት ሲባልእነዚህን ነገሮች ሁሉ ሊገነዘብ ይገባል፡፡በቅድሚያ ለራሱ ከመታመንና ፈሪሃ እግዚአብሔር ካለዉ ለሌሎች ለመታን አይቸግርም፡፡

ለሁሉም ታማኝ በመሆን የእግዚአብሔርን መንግስት ለመዉረስ እንዲያበቃን የ አምላካችን ቅዱስ ፈቃድ ይሁንልን፡፡አሜን

Saturday, April 6, 2013

ደብረ ዘይት


ምንጭ፦ አትሮንስ - የዲያቆን ኤርምያስ ነቢዩ ገጽ  

             ማህበረ ቅዱሳን ድኅረ ገጽ



በአባ ዘሚካኤል ደሬሳ
የዓለሙ ፍጻሜ ምልክቱ ምንድ ነው?/ማቴ. 24፣3/

በዓቢይ ጾም ውስጥ ካሉት ሳምንታት ደብረ ዘይት 5ኛው ሳምንት ላይ ይውላል፡፡ ደብረ ዘይት ትርጉሙ የወይራ ዛፍ ተራራ ማለት ሲሆን፣ ይህም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኢየሩሳሌም በሚገኘው በደብረ ዘይት ተራራ ቅዱሳን ሐዋርያት” የዓለሙ ፍጻሜስ ምልክቱ ምንድነው?”/ማቴ. 24፣3/ ብለው ጠይቀውት እርሱም የማይቀረውን የዓለም ፍጻሜና አስቀድመው የሚፈጸሙ ምልክቶችን አስረድቷቸዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያንም ይህንኑ በደብረ ዘይት ሳምንት ታስበዋለች፤ ለምእመናኑም ከዘመኑ ሁኔታ አንጻር በመጻሕፍት የተጠቀሱትን የትንቢት ምልክቶቹን ከተግባራዊ የዓለም ክንዋኔዎች አንጻር በማገናዘብ ታስተምራለች፡፡ በመሆኑም በቤተ ክርስቲያናችን በደብረ ዘይት ሳምንት ምጽአትን አስመልክቶ የሚነገሩ ምስጢራት እጅግ ሰፊ ናቸው፡፡ ነገር ግን በዚህ ጽሑፍ በመጠኑ የምናየው ከቅዱሳት መጻሕፍት አንጻር በዓለም እየተከሰቱ ካሉ ወቅታዊ ምልክቶች ጋር በማገናዘብ ይሆናል፡፡

የሰው ልጅ ከሥነ ፍጥረት መነሻ ጀምሮ ስለ ራሱ መጨረሻና ስለ ዓለም ፍጻሜ ምንነት ማወቅን እንደሚሻ ቅዱሳት መጻሕፍት ያስረዱናል፡፡ ከነዚህም በተለይ ቤተ ክርስቲያን በደብረ ዘይት እለት የምታስተምረው፤ ቅዱሳን ሐዋርያት’ የዓለሙ ፍሳሜስ ምልክቱ ምንድነው?/ማቴ. 24፥3/’ በማለት የጠየቁት ጥያቄ ቅድሚያ ይሰጠዋል፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያት ከመለሰላቸው ዋናውና ቀዳሚው የምጽአቱ ምልክት የሐሳዊ መሲህ መምጣት ነው፡፡ ሐሳዊ መሲሕ ማለት በቀጥታ ትርጉሙ ሐሰተኛ የሆነ በስሙ ማለትም በኢየሱስ፣ በክርስቶስ፣ በአምላክ ስም የሚመጣ የክርስቶስ ተቃዋሚ ማለት ነው፡፡ ትርጉሙን አስፍተን ስናየው፣ ደግሞ ከሃይማኖት ጋር ተያያዥ የሆኑና ያልሆኑ በዓለም እየተካሄዱ ያሉ ሐሰተኛ ጉዳዮችንና የጥፋት መንገዶችን ያጠቃልላል፡፡ የሐሳዊ መሲሕ የጥፋት ሥራዎች ሳያውቁም ሆነ
በተለይ ሆን ብለው በዓለማውያንና በክፉ መናፍስት ተከታዮች እየተፈለሰፉ በሚከሰቱ ሁኔታዎች የሚካሄዱ ናቸው፡፡ ከእግዚአብሔር የተገኙ የሃይማኖት የሥነ ተፈጥሮ የጋብቻና የመሳሰሉ ድንበሮች ማፍለስን ዓላማ ያደረጉ፤ እንዲሁም መንፈሳዊ ባህል፣ ሰብአዊ ክብርና የእድሜ፣ የቅደም ተከተል ትስስርና ክብር እንዲጠፋ የሚሠሩ ሁሉ ከሐሳዊ መሲሕ መደብና ከዓለም ፍጻሜ ምልክትአንጻር የሚታዩ ናቸው፡፡ በዝርዝር ለማየት የሚከተሉትን ነጥቦች እንመልከት፣

1. የሃይማኖት ድንበርን ማፍለስ፡- ”አባቶችህ ያኖሩትን /የሠሩትን/ የቀድሞውን የድንበር ምልክት አትፍልስ” ምሳ.22፥28፣ 23፥10 አፈጻጸሙ ሰዎች የእግዚአብሔርን

Tuesday, April 2, 2013

እግዚአብሔርን መፍራት



& ለሥጋህ ፈዉስ ይሆንልሃል/ምሳ 3-7/
& ዘመንን ያረዝማል/ምሳ 10-27/
& ጠንካራ መታመኛ ነዉ/ምሳ 14-27/
& ሰዉን ከክፋት ይመልሳል/ምሳ 19-23/
& ሰዉን ወደ ህይወት ይመራል/ምሳ 19-23/
& ባለጠግነትና ክብር ነዉ/ምሳ 19-23/
& የጥበብ ሁሉ መጀመሪያ ነዉ/ምሳ 7-1/
                                     ከ ገብረ ዮሐንስ ተፈራ
                  ከ አሶሳ ደ/ም/ቅ/ገብርኤል ሰ/ት/ቤ/ት
ወስብሐት ለ እግዚአብሔር

ዕድሜህ ስንት ነዉ?



ስንት ዓመት ኖረሀል?
ምን አሳልፈሀል
ምንስ ቀርቶብሃል?
ዕንደ ያዕቆብ እየዉ
ዞረህ ወደ ኋላ
ስትቀርብ ሚርቅህን
የዕድሜህን ጥላ
ስንት ዓመት አለፈህ
ጌታህን ካወቅኸዉ
ተመችተኸዋል
ወይስ ቆረቆርኸዉ
እንዲያዉ ለማደግህ
ምን ምልክት አለህ
የኃጢአት ጡጦህን
ጣልከዉ ትጠባለህ?
ዛሬም እንደ አምናዉ
ዳዴን አልጨረስክም?
ማደግህ እንዲታወቅ
መራመድ አልቻልክም?
አሊያማ ከደፈርክ
አደኩኝ ለማለት
ስንት ዓመት ኖረሀል
ምንስ ሠራህበት
                       ዘፍ 47-8
             ከወርቅነሽ ቱፋ

ጾም ለምን?(ክፍል ሁለት)



ጾም ወደ እግዚአብሔር ለመመለስና ንስሓ ለመግባት ይጠቅማል
ክብር ምስጋና ይግባዉና እግዚአብሔር በምክንያተ ኃጢአት ከእርሱ ስንለይና ከክብር ስንርቅ ወደእርሱ እንመለስ ዘንድ ይሻል፡፡እንዴት መመለስ እንዳለብን የነገረን እንዲህ በማለት ነዉ‹‹በፍጹም ልባችሁ በጾም በለቅሶና በዋይታ ወደ እኔ ተመለሱ››ኢዩ2-12 ወደ እግዚአብሔር የምንመለሰዉ በጾምና በጸሎት ነዉ፡፡ጾም ለሥርየተ አበሳ ይጾማል፡፡‹‹ወሀበነ ጾመ ለንስሓ በዘይሠረይ ኃጢአት››እንዲል ጾም በደልን አምኖ ጥፋትን ተቀብሎ በፍጹም ትሕትና ወደ እግዚአብሔር በመቅረብ በድያለሁና ማረኝ ይቅር በለኝ በማለት ምሕረቱንና ይቅርታዉን የሚያገኙበት መሣሪያ ነዉ፡፡
ጾም ፊትን ወደ እግዚአብሔር ማቅናት እንደሆነ በሰብአ ነነዌ ታዉቋል እነዚህ ሰዎች ወደ እግዚአብሔር የተመለሱት በጾም ነዉና፡፡ኃጢአታቸዉ እጅጉን ገዝፎ ቅድመ እግዚአብሔር ስለደረሰ የጌትነቱ ጨንገር ከመምጣቱ አስቀድሞ ንስሓ እንዲገቡ መሐሪ እግዚአብሔር ነብዩ ዮናስን ላከላቸዉ፡፡ሕዝቡም የነቢዩ ስብከትን ሰምተዉ በክፉ ስራቸዉ ተጸጽተዉ ከሊሒቅ እስከ ደቂቅ ማቅ ለበሱ አመድንም በራሳቸዉ ነሰነሱ፡፡ንጉሱም ከዙፋኑ ወርዶ መጎናጸፊዉን አዉልቆ ማቅ ለብሶ በአመድ ላይ ተቀመጠ፡፡አዕምሮ ጠባይዕ ያላደፈባቸዉ ሕጻናትና እንስሳትንም የንስሓቸዉ ተካፋዮች እንዲሆኑ አደረጉ፡፡በዚህ ጊዜ የፍጥረቱን መዳን እንጂ ጥፋቱን የማይወድ እግዚአብሔር ቁጣዉን በትዕግስት መዓቱን በምህረት መልሶ በይቅርታ ጎበኛቸዉ ከጠቀጣዉ መቅሠፍት አዳናቸዉ፡፡ዮና 3-5-10
ወደ እግዚአብሔር በጾም በጸሎት የተመለሱ ድኅነትን እንዳገኙ ሁሉ ያልተመለሱት ደግሞ ጠፍተዋል፡፡ለምሳሌ ሰብአ ሰዶም ገሞራ እንደ ነነዌ ሰዎች በጾም ወደ እግዚአብሔር ባለመመለሳቸዉ እሳት ከሰማይ ወርዶ አቃጥሎ አጥፍቷቸዋል፡፡ዘፍ 19-23
ጾም ኃይለ አጋንንትን ለማድከም ጸብአ አጋንንትን ለማብረድና ለማሶገድ ይጠቅማል
ከጽልመት አበጋዝ ግዝፈ አካል ከሌላቸዉ አጋንንት ጋር በምናደርገዉ ዉጊያ ጾም አይነተኛ መሳሪያ ነዉ፡፡አጋንንት ስለተለያዩ ምክንያቶች ትሩፋት መስራት እስኪሳነን ድረስ ይዋጉ ዘንድ ይታዘዛሉ፡፡የሚዋጉንም ነፍሳችን ጾርን ትማር ዘንድ እግዚአብሔርን መፍራታችን መዉደዳችን ይታወቅ ዘንድ ነዉ፡፡
ጌታችን መጾም ሳያስፈልገዉ የጾመዉ በጾም መሳሪያነት ዲያብሎስን ድል ታደርጋላችሁ ሲለን ነዉ፡፡እርሱ ድል አድርጎለታልና ካልጾሙ ካልጸለዩ ሰይጣንን ድል ማድረግ እንደማይቻል ጌታ አስተምሮናል፡፡አንድ ልጁ የታመመበት ሰዉ ሐዋርያት ልጁን እንዲያድኑለት ጠይቋቸዉ ሊያድኑለት አልተቻላቸዉም፡፡ያም ሰዉ ጌታን ‹‹መምህር ሆይ ዲዳ መንፈስ ያደረበትን ልጄን ወደ አንተ አምጥቼአለሁ በዚያም ስፍራ ሁሉ ይጥለዋል አረፋም ይዳፍቃል ጥርሱንም ያፋጫል አጋንንቱን እንዲያወጡለት ለደቀ መዛሙርትህ ነገርኋቸዉ ሊያወጡት አልቻሉም››አለዉ በዚህን ጊዜ ጌታ ለደቀ መዛሙርቱ ስለ እምነታቸዉ መጉደል ከገሠጻቸዉ በኋላ ወደ እኔ አምጡት አላቸዉ፡፡ወደ እርሱም ባመጡት ጊዜ ያ መንፈስ ወዲያዉ አንፈራገጠዉ፡፡
ርኩሱን መንፈስ ከገሰጸ በኋላ‹‹አንተ ዲዳ ደንቆሮም መንፈስ እኔ አዝሃለሁ ከእርሱ ዉጣ እንግዲህም አትግባበት››በማለት ተረፈ ደዌ እንዳይኖርበት ሙሉ ጤንነትን ሰጠዉ ቅዱሳን ሐዋርያት ጋኔኑን ማስወጣት ባለመቻላቸዉ የጎደላቸዉን ለማወቅና ስህተታቸዉን ለማረም ሽተዉ እኛ ልናሶጣዉና ልጁን ልናድነዉ ያልተቻለን ስለምንድር ነዉ?በማለት ጠይቀዉታል፡፡እርሱም‹‹ዝንቱ ዘመድ ኢይወጽእ ዘእንበለ በጾም ወበጸሎት ይህ ዓይነቱ አብሮ አደግ ጋኔን በጾምና በጸሎት ካልሆነ በቀር ይወጣም››አላቸዉ ማር 9-29
ስለሆነም ጾምን በሥርዓት ወስኖ በሃይማኖት መጾም ለክርስቲያኖች ዲያብሎስን ድል የሚነሱበት ዐብይ ኃይል ነዉ፡፡
   
  ጾም የበጎ ምግባር መገኛ መጀመሪያ ነዉ
‹‹ከኃጢአት ጾር አንዱን ድል ለመንሳት በጾም መድከም የስራ ሁሉ መጀመሪያ ነዉ፡፡››ማር ይስሐቅ አንቀጽ 9 ምዕ 6፡፡መብል ለኃጣዉእ መሰረት እንደሆነ እንደዚሁም ጾም ለምግባር ለትሩፋት መሰረት ነዉ፡፡
ጾም ገንዘብ ያደረጉትን መንፈሳዊ ግብር ያስፈጽማቸዋል፡፡ጾምን የሚያቃልል ሰዉ ሌላውን ትሩፋት ከመስራት ቸል ይላል፤ይደክማል፡የሐኬት ምልክትነትም ኃጢአትን ወደ ሰዉነቱ መርታ ታደርሳለች፡፡በጎ የሆነዉን ነገር ከራሱ ያርቃል፡፡ስለ ማሸነፍ ፋንታ ጾሩ ነጉዶ ይመጣበታል፡፡
ጾም ለስብከተ ወንጌል መስፋፋት አስፈላጊ ነዉ፡፡በስራ አምላካቸዉን ለመምሰል የወጡ ሁሉ ጾምን የስራቸዉ መጀመሪያ አድርገዋል ምክንያቱም ጾም ከእግዚአብሔር የተሰጎደ(የተሰጠ)ጋሻ ነው፡፡ቅዱሳን ሐዋርያት ወደየ ክፍለ አሕጉሩ ለስብከተ ወንጌል ከመለያየታቸዉ በቅድሚያ ጌታን አብነት አድርገዉ አንድ ሆነዉ ጾመዋል፡፡ስለሆነም ማንኛዉም ስራ ከመጀመራችን በፊት በጾም ፈቃደ እግዚአብሔን መጠየቅ ይገባናል ይህም ልንሰራዉ ያሰብነዉን ስራ በአግባቡ ለመወጣት ያስችለናል፡፡
     ጾም ሕይወተ ዘለዓለምን ለመዉረስ ይረዳናል
ጾም የጽድቅ መሠረት የገነት በር ነዉ፡፡ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአንቀጸ ብጹዓን‹‹ ይርኅቡ ወይጸምዑ በእንተ ጽድቅ አብዝተንማ ከተመገብን ሰዉነታችን ገትቶ ወስኖ ማኖር እንደምን ይቻለናል ብለዉ ከሚበሉት ከሚጠጡት ከፍለዉ የሚራቡ የሚጠሙ ንዑዳን ክቡራን ናቸዉ›› ብሏል፡፡ማቴ 5-6  የሰዉ ልጅ ኃጢአት ካልሰራ ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየዉም፡፡ቤተ መቅደስ ልቦናዉ ከመተዳደፍ የተለየ ከሆነ በእግዚአብሔር ቸርነት ርስቱን ይወርሳል ከዚህም በላይ ለፍቅሩ የሚሳሱ አንድም በመማር በማስተማር በሃይማኖት በምናኔ በንስሓ የሚራቡ ሰዎች ንዑዳን ክቡራን ናቸዉ‹‹ይጠግባሉና››አለ እዚህ ላይ የርኃብ አጸፋዉ ጥጋብ ስለሆነ ይጠግባሉ ሲል  መንግስተ ሰማያትን ይወርሳሉ ማለቱ ነዉ፡፡ ይቀጥላል……………….