ታማኝነት ማለት ምሎ የማይከዳ፤አደራ የማያጠፋ፤የያዘዉን በቀላሉ የማይለቅ፤የማያወላዉል፤ለምስክርነት የሚበቃ ማለት ነዉ፡፡ታማኝ ሰዉ የሚያምነዉንና መልካም ነዉ የሚለዉን ይናገራል የሚናገረዉንም ይሠራል፡፡ባሠማሩትም ሥራ ላይ በሚቻለዉ ሁሉ እንከን ሳያስገባ ጠብቆ ይገኛል፡፡በኃላፊነት ቦታ ቢያስቀምጡት ያለምንም አድሎዎና ወገናዊነት ያስተዳድራል፡፡
አንዳንድ ሰዎች ግን ታማኝነትን እንደቀላል ነገር ስለሚመለከቱት እምበዛም ትኩረትአይሰጡትም፡፡ስለዚህም በሥራቸዉ፤በትዳራቸዉ፤በ አጠቃላይ ኑሯቸዉ ወዘተ…ታማኝ ለመሆን አይጥሩም፡፡ነገር ግን ታማኝነት ከሰዉና ከእግዚአብሔር ጋር የምንገናኝበትና ማንነታችን(ክርስቲያናዊ ሕይወታችን)የሚለካበት ሚዛን ነዉ፡፡በመሆኑም አንድ ክርስቲያን በኑሮዉ ሁሉ በሚከተሉት ነገሮች ታማኝነቱን ሊገልጥ ይገባዋል፡፡
ለራስ ታማኝ መሆን
ለራሳቸዉ ታማኝ ያልሆኑ ሰዎች በተናገሩት አይጸኑም፡፡እንደ ዉኃ ላይ ኩበት ሁል ጊዜ ወዲያና ወዲህ እንደዋለሉ ይኖራሉ፡፡ለጊዜዉ የሚያገኗቸዉን ጥቅሞች በማሰብና በአካባቢያቸዉም ተፅዕኖ ምክንያት በዉሳኔአቸዉ አይረጉም፡፡ስለዚህ‹‹አደርጋለሁ››ብለዉ የሚወስኑትና የሚያደርጉት አይገናኝም፡፡የሚያስፈልጋቸዉንና የማያስፈልጋቸዉን ለመለየት ይቸግራሉ፡፡ሌሎችንም ለማመን ስለሚከብዳቸዉ ሕይወታቸዉ በጥርጥር የተመላ ይሆናል፡፡ስለዚህ ክርስቲያን ለሌሎች ከመታመኑ በፊት በቅድሚያ ለራሱ ሊታመን ይገባዋል፡፡ሁል ጊዜም የሌሎችን ይሉኝታ እያሰበ ብቻ ሳይሆን እዉነትን ይዞ መጓዝ ይኖርበታል፡፡እንደዚያ ከሆነ በተናገረዉ ይጸናል፤አይዋሽም፤ለጊዚያዊ ጥቅም ራሱን አሳልፎ አይሰጥም፡፡
ለእግዚአብሔር ታማኝ በመሆን
እግዚአብሔር ለቅዱሳን የገባዉን ቃል ኪዳን የሚያከብርና የሚፈጽም በቃሉ የታመነ ነዉ፡፡እንደዚሁም የእርሱ የሆኑ ሁሉ ታማኝ እንዲሆን ይፈልጋል፡፡በመሆኑም ክርስቲያኖች የክርስቶስ ሙሽሮች ነንና በፍጹም ፍቅር ለእርሱ ልንታመን ይገባናል፡፡ልባችንና አጠቃላይ ሰዉነታችንን ለእግዚአብሔር ፍቅር አሳልፈን ከሰጠን ከሁሉም በላይ ለእርሱ ያለንን ፍቅር ስለምናስቀድም ለመታመን አንቸገርም፡፡ቃሉን ለማክበርና ትዕዛዙን ለመፈጸም እስከመጨረሻዉም በቤቱ ለመጽናት እንችላለን፡፡ቅዱስ ዮሴፍ በግብጽ በስደት ሲኖር የጲጥፋራ ሚስት ኃጢያጥ እንዲፈጽም ትገፋፋዉ ነበር፡፡ተመልካች ሰዉ በሌለበት ሰዓት ስታስጨንቀዉ‹‹እንዴት በ እግዚአብሔር ፊት ኃጢያትን እሰራለሁ?››በማለት ለፈጣሪዉ ያለዉን ፍቅርና ታማኝነት በቃሉ ብቻ ሳይሆን በተግባርም ገለጸ፡፡ዘፍ 39-9፡፡ዮሴፍ በዚህን ጊዜ ኃጢያትን እንቢ በማለቱ የሚደርስበት ስቃይ አልታየዉም ከሁሉም በላይ የሆነዉና በስደትም ያልተለየዉ የ እግዚአብሔር ፍቅር እንጅ!በዘመናችን ግን ብዙ ሰዎች የሚገዙት መግባት መዉጣታቸዉን ለሚቆጣጠረዉና ለአፍታ እንኳን ለማይለያቸዉ ለእግዚአብሔር ሳይሆን ለሰዎች ነዉ፡፡ስለዚህም ብዙ ወንጀሎችና ኃጥያቶች የሚፈጸሙት ሰዎች አያዩኝም ተብሎ በሚታሰብባቸዉ በጨለማ ጊዜያት ነዉ፡፡ፈሪሃ እግዚአብሔር ሳይኖራቸዉና ፍቅሩ ሳያስገድዳቸዉ በአካባቢአቸዉ ያሉትን ሰዎች ብቻ በመፍራት የሚኖሩ ሰዎች ብዙዉን ጊዜ ተደብቀዉ ይበድላሉ፤ይዋሻሉ፤ጉቦ ይሰጣሉ፤ይቀበላሉ፤ አደራ ያጎድላሉ ወዘተ…….ስለዚህ ክርስቲያን የሚሰራዉን ሁሉ ለእግዚአብሔር ፍቅር ብሎ ፈሪሃ እግዚአብሔር ኖሮት ከሠራ በተሰማራበት ሁሉ ታማኝነት የ እግዚአብሔር ፍቅር መለኪያና ለታላቅ ክብሮትም የሚያበቃ ነዉ፡፡ መዝ 36-4 ሮሜ 8-35
ለሎች ሰዎች ታማኝ በመሆን
ክርስቲያን በመቅረዝ ላይ ያለ መብራት ነዉና ለራሱ ብቻ አይኖርም፡፡ብርሃኑን ለሌሎች ያበራል፡፡ስለዚህ በዕለት ለዕለት ኑሮዉ ከሰዎች ጋር ስለሚገናኝ በተሰማራበት ሁሉ ታማኝ ሊሆን ያስፈልጋል፡፡በተለይም እዉነተኛ ፍቅር በልቡ ያለዉና ሌሎችን እንደራሱ አድርጎ ለሚወድ ሰዉ ታማኝነት ምግባሩ ነዉ፡፡አደራ ቢቀበል አይክድም፤የራሱን ጥቅም አስቀድሞ አይዋሽም፤በሀሰት አይመሰክርም፤የገባዉን ቃል ኪዳን አያፈርስም፡፡ለሌሎች ታማኝ መሆን የሚጀምረዉ ከአነስተኛና እኛ ቀላላ አድርገን ከምንገምተው ነገር በመነሳት ነዉ፡፡የተሰጠችን አነስተኛ አደራ በመጠበቅ ምስጢር መያዝ ወዘተ..እንደዚህ በጥቂቱ የታመነ በብዙ ይሾማል ማቴ25-21 ሌላዉ የዘመናችን ችግር የብዙ ሰዎች በትዳራቸዉ ታምኖ አለመገኝት ነዉ፡፡ትዳር ያልመሰረቱ ወጣቶች እነረኳን(ለምን ትዳር አትመሰርትም?አትመሰርችም?)ተብለዉ ሲጠየቁ‹‹የሚታመን ሰዉ አለ ብላችሁ ነዉ?››ይሆናል መልሳቸዉ፡፡በትዳር ላይ ያለዉ ዉስልትና አለመተማመን ጋብቻን ያህል በብዙዎች ዘንድ የሚያስመርር አድርጎታል፡፡ሌላዉ ችግር ደግሞ በተሰማሩበት ወይም በተሾሙበት የስራ መስክ ታማን ሆኖ አለመገኝት ነዉ፡፡ምዝበራ፤ጉቦኝነትና አድልዎ በ የጊዜዉ የሚሰሙና ብዙ ሰዎች የሚዎድቁበት ጉዳይ ነዉ፡፡እንግዲህ አንድ ክርሰቲያን ታማኝ መሆን አለበት ሲባልእነዚህን ነገሮች ሁሉ ሊገነዘብ ይገባል፡፡በቅድሚያ ለራሱ ከመታመንና ፈሪሃ እግዚአብሔር ካለዉ ለሌሎች ለመታን አይቸግርም፡፡
ለሁሉም ታማኝ በመሆን የእግዚአብሔርን መንግስት ለመዉረስ እንዲያበቃን የ አምላካችን ቅዱስ ፈቃድ ይሁንልን፡፡አሜን
No comments:
Post a Comment