Saturday, May 4, 2013

ክርስቶስ ካልተነሳ እምነታችሁ ከንቱ ነው!!!



መልዕክት ዘአቡን ቤት ቅዱስ ገብርኤል ሰንበት ት/ቤት፤ጎንደር

‹‹……ክርስቶስ ካልተነሳ  እምነታችሁ ከንቱ ነው፡፡….››1ኛቆሮ15፤14
       አሁን ግን ክርስቶስ ላንቀላፉት በኩራት ሆኖ ከሙታን ተነስቷል ፡፡ሞት በሰው በኩል ስለመጣ ትንሳኤ ሙታን በሰው በኩል ሁኗል ፡፡1ቆሮ 15፤20 የጎሰቆለውን የሰውን ህይወት ያድሰው ዘንድ ወደ ዓለም የመጣው ተቀደሚ እና ተከታይ የሌለው የእግዚአብሔር አብ የባህርይ ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ የሞትን እንቆቅልሽ በሞቱ ፤ሞተን እንዳንቀር በትንሳኤው አረጋግጦልናል፡፡ትንሳኤ ማለት ተንስኦ ካለው የግዕዝ ግስ የተወረሰ ሲሆን የቃሉ ትርጉም መነሳት ፤አነሳ ማለት ነው፡፡በሌላ አጠራር በዓሉ ፋሲካ ይባላል ፡፡በዘመነ ኦሪት ይከበር የነበረው የፋሲካ በዓል እስራኤል ዘስጋ ከባርነት ቀንበር ወደ ነጻነት የተላለፉበት ከሀዘን ወደ ደስታ የተሸጋገሩበት በዓል ነው፡፡ዘፀ12፤14
      ፋሲካ ማለት መሸጋገር ማለት ነው፡፡ዘፀ12፤14 የተጠቀሰው ታሪክ መልዐከ ሞት የዕብራውያንን ቤት እያለፈ ግብጻውያንን በሞት በመቅጣቱ ይህንን ቀን ስጋዊ ነጻነትን የተጎናጸፍንበት ስልሆነ ፋሲካ ብለው ያከብሩታል፡፡የደሙ ምልክት ያለበትን ቤት እያለፈ ሌሎችን መግደል…… በኋለኛው ዘመን ከልዕል መንበሩ ወርዶ በደሙ የሲኦልን ባህር የአዳምን ዘር በማሻገሩ ከኃጢአት ወደ ጽድቅ ከአሳር ወደ ክብር የተሸጋገርንበት በዓል ነው እና ፋሲካ ተብሏል፡፡(ምድር ፋሲካን ተደርጋለች…በክርስቶስ ደም ስለታጠበች )እንዳለ ቅ/ያሬድ በድጓ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዲያቢሎስ ግርማ በሲኦል ከተማ በእሳት ወላፈን ሲገረፍ የኖረዉን ሰዉ ለማዳን በአይሁድ ጅራፍ ተገረፈ፡፡ታላቅ መከራንም ተቀበለ፡፡ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ በቅዳሴው‹‹…የማይታመመውን የእርሱን ህማም እንናገራለን….የማይሞተውን የእርሱን ሞት እንናገራለን….ሁሉን የያዘውን ያዙት…የህያው አምልክን ልጅ አሰሩት….በቁጣ ጎተቱት……በፍቅር ተከተላቸው…..ኃጢአትን ይቅር የሚልውን ሀጥእ አሉት በመኳንንት የሚፍረደውን በእርሱ ላይ ፈረዱበት ….ለሱራፌል ዘውድ የሚያቀዳጃቸውን የሾህ አክሊል አቀዳጁት…ለኪሩቤል የግርማ ፤ልብስ የሚያለብሳቸውን ለመዘበት ቀይ ግምጃ አለበሱት……አዳምን የፈጠሩ እጆች በመስቀል ቀኖት ተቸነከሩ….በገነት የተመላለሱ እግሮቹ…..በመስቀል ቀኖት ተቸነከሩ…..በአዳም ፊት የህይወት መንፈስ እፍ ያለ አፍ ከሀሞት ጋር የተቀላቀለ የኮመጠጠ መራራን ጠጣ ……..እንደዚህ ያለ ትህትና እንደምን ያለ ትህትና ነው? …..እንደዚህ ያለ ትዕግስት እንደምን ያለ ትዕግስት ነው? ….እንደዚህ ያለ ዝምታ እንደምን ያለ ዝምታ ነው? ….እንደዚህ ያለ ሰውን ማፍቀር እንደምን ያለ ፍቅር  ነው?….ፍቅር የአምላክን ልጅ ከዙፋኑ ሳበው….እስከሞትም አደረሰው……..›› በማለት የእለተ ዓርቡን መከራ ይገልጻል ፡፡ጌታችን ከሞተ በኋላ በአዲስ መቃብር ጨምርው ቀበሩት በሦስተኛው ቀን እንደተናገረው መግነዝ ፍቱልኝ ….መቃብር ክፈቱልኝ ሳይል ተስፋ አስቆርጦን የነበረውን ሞት ድል ነስቶ ተነሳ፡፡እኛም እንዲህ እንድንል አበቃን፡፡‹‹……ሞት ሆይ መውጊያህ የታል..ሲኦል ሆይ ድል መንሳትህ የታል …..››.1ኛ ቆሮ15፤55 ብለን በህይወት ላይ ቆመን በሞት ላይ እንድንዘብት አደረገን፡፡ከመቃብር በስተጀርባ የክብር ትንሳኤ እንዳለ ነገረን ፡፡ቅዱስ ጳውሎስ እንደመሰከረው የጌታችን ትንሳኤ ለእምነታችን መሠረት ነው፡፡‹‹….ክርስቶስ ካልተነሳ እንግዲያስ ስብከታችን ከንቱ ነው…..እምነታችሁም ደግሞ ከንቱ ናት …›› በማለት የክርስቶስ ትንሳኤ  ለምናምነው የክርስትና እምነት መሠረት መሆኑን አስረድቷል፡፡1ቆሮ 15፤14

በጌታችን መቃብር አጠገብ ልናስተውለው የሚጋብን ነገር አለ፡፡አይሁዳውያን ሙቶ የሚቀር መስሏቸው ታላቅ ድንጋይ በመቃሩ ደጃፍ ላይ አንከባለው ዘግተውበት ነበር፡፡ማቴ27፤60 የጌታን መቃብር ሊያዩ የሄዱ ሴቶች እንዲህ አሉ ‹‹…ድንጋዩን ማን ያንከባልልናል…?.››ማር16፤3
¤  ይህ ድንጋይ ቃየል አቤልን የገደለበት ዘፍ4፤1-8 ባቢሎናውያን በሰናኦር ላይ ያቆሙትና እግዚአብሔርን የፈተኑበት የትዕቢት ድንጋይ ዘፍ11፤1-9 ዲያቢሎስ ለጌታችን ደቦ እንዲያደርገው ያቀረበለት የፈተና ድንጋይ ማቴ4፤3 በአጠቃላይ ይህ ድንጋይ መላውን የዓለምን ዘር ያስጨነቀ ፤ያሰቃየ ፤ያስለቀሰ፤ያስተከዘ ሞት ነበር ፡፡መቃበሩ አጠገብ የደረሱት ቅዱሳት አንስትም ያስጨነቃቸው ይኸው ነበር፡፡ ሞት ይይዘው ዘንድ የማይቻል ኃያላን ነን የሚሉት በኃይሉ የሚመረምር በአባቱም ዘንድ በመላእክቱም ዘንድ ፤በሰውም ዘንድ የተመሰገነ የጌትነቱ ክብር በሰማይና በምድር የመላ ወደ ሰማይ ሲያርግ ደም ግባቱ ደም ግባቱ ሰማያትን ያለበሰው የሞትን እንቆቅልሽ በሞቱ የፈታው መድኃኔዓለም  ክርስቶስ ነው፡፡ዲያቢሎስ ይህንን ከቃየል ጀምሮ አቤልን ያስገደለበት ድንጋይ በጌታችን መቃብር ብቻ ላይ ወስኖት አልቀረም፡፡ በዚሁ ዘመንም ይጠቀምበታል፡፡የበደልናኃጢአት ድንጋይ ፤ተስፋ የሚያስቆርጥ ድንጋይ፤የኑፋቄ ድንጋይ፤በሰው ልጆች ላይ እየጫነው ይገኛል፡፡ነገር ግን ወደ ሞተልን አምላክ ብንቀርብ ይህን ድንጋይ ከላያችን ላይ ያነሳዋል፡፡ማቴ11፤28 በአጠቃላይ
        የክርስቶስ ትንሳኤ ለዕምነታችን መሠረት ነው፡፡1ቆሮ15፤12
        ክብራችን ነው፡፡ሉቃ24፤13
        ሙተን እንዳንቀር የተበሰረበት ነው፡፡ዮሐ11፤25
        ጠላት የተዋረደበት ነው፡፡ቆላ2፤15
        ሲኦል ባዶውን የቀረበት ነው፡፡1ጴጥ3፤18-20
        ሞት የሞተበት ታላቅ በዓል ነው፡፡1ቆሮ15፤55
አምላክ ወልደ አምላክ ሞተ ፤የሰውን ልጅ ከሞት ያደን ዘንድ ሞተ ፤ሞት በሰው በኩል መጥቶ ነበርና ሰው ሁኖ ሞቶ ሞትን ሻረ ፤ለዚህ ነው ሐዋርያው ክርስቶስ ካልተነሳ እምነታችሁ ከንቱ ናት ያለው፡፡በመሆኑም ይህንን ታላቅ በዓል ስናከበር
v  በደዌ ዳኛ ፤በአልጋ ቁራኛ ተይዘው አስታማሚ በማጣት የሚሰቃዩት ህሙማን
v  እናት አባታቸውን በሞት ተነጥቀው አሰዳጊ አልባ የቀሩትና ለጎዳና ተዳዳሪነት የተዳረጉት ህጻናትን
v  ጧሪ ቀባሪ በማጣት ቤታቸው ፈርሶ ለልመና እጅ የሰጡትን አረጋውያን
v  በስር እየማቀቁ ያሉ የህግ ታራሚዎችን
v  ንብረታቸውን በትነው‹‹ ነገ ያልፍልኛል›› በማለት  ከአንዱ ቀየ ወደ ሌላው ቀየ ……ከአንዱ ሀገር ወደ ሌላው ሀገር የሚባዝኑትን ስደተኞችን በማሰብና ለእነዚህ ወገኖቻችን አቅማች እንደፈቀደ የምንችለውን ሁሉ በማድረግ ሊሆን ይገባል ፡፡
‹‹ በሞቱ ያዳነን …..በስሙ ያከበረን መድኃኔዓለም ክርስቶስ ከእናቱ ከቅድስት ድንግል ማርያም ጋር የተመሰገነ ይሁን ››
‹‹የሰላም በዓል ያድርግልን……ወስብሐት ለእግዚአብሔር…….››

No comments:

Post a Comment