Tuesday, March 12, 2013

የሰንበት ትምህርት ቤቱ አመሰራረት


ደብረ ምሕረት አቡን ቤት ቅዱስ ገብርኤል ሰንበት ትምህርት ቤት በ1974 ዓ.ም በቀኝ ጌታ ሞገስ መርሻ አማካኝነት ተመሰረተ።


በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!


    
         ምንም እንኳን ሰንበት ት/ቤታችን ሲመሰረትም ሆን ከዚያም ቀደም ብሎ ጎንደር ውስጥ ከብዙ ተጽዕኖዎች ጋር የሰንበት ት/ቤት እንቅስቃሴ ቢኖርም ያን ያህል የተጠናከረ እና ስር የሰደደ ነበር ለማለት አያስደፍርም ምክንያቱም በጊዜው መንበረ ስልጣኑን ተቆናጦ የነበረው ወታደራዊ ፣መንግስት ያራምድ የነበረው ማርክሲስት ሌኒኒስት አይዲዮሎጅ ሀልዎተ እግዚአብሔርን ያስክድ ስለነበር በየእምነት  ተቋማቱ ቤተ ክርስትያናችን ጨምሮ ህብረተሰቡ የዕምነቱን ነጻነት እንደልቡ እንዳያራምድ ገድቦት ስለ ነበር ነው፡፡በዚህም ሳቢያ የወጣቶችን በቤተ ክርስትያን መሰብሰብን በዓይነ ቁራኛ ነበር የሚከታተለው ፡፤በተለይም በአኢወማ እና በአኢሴማ የታቀፉ ወጣቶች ከሆኑ ስርዐተ አምልኮ ሲፈጽሙ መገኘት ወነጀልም ነበር፡፡አንደኛው ምክንያት ይህ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በቤተክርስቲያኗ የተጠናከረ የወንጌል አገልግሎት አለመሰጠቱ እና የቤተክርስቲያኗ አስተዳደር ወጣቱን በማቅረብ ዙሪያ የነበረው እንቅስቃሴ ልል መሆኑ ነበር ፡፡እንግዲህ በእነዚህ አጣብቂኝ ጊዜያት ዉስጥ ነው የአቡን ቤት ቅዱስ ገብርኤል ሰንበት ት/ቤት በ1974 ዓ/ም  በይፋ የተመሰረተው፡፤ለሰንበት ት/ቤቱ መመስረት ምክንያት የሆኑት ደግሞ  በደብሩ የአብነት ትምህበተጠናከረ ሁኔታ ይሰጡ የነበሩት ቀኝ ጌታ ሞገስ መርሻ ናቸው፡፡
             መምህሩ ፍቅረ እግዚአብሔር አገብሯቸው ጥቂት ሆነው ቅዳሜ እና እሁድ ኢ-መደበኛ በሆነ መልኩ በመሰባሰብ እርስ በእርስ ይማማሩ የነበሩትን ወጣቶች ቀርቦ በማበረታታት ከመንፈሳዊ እና አባታዊ ምክር በተጨማሪ መሰረታዊ የቤተ ክርስቲያን
ትምህርት በማስተማር የወጣቶችን ስብስብ መልክ አስያዙት ከጥቂት ወራት በኋላ ስብስቡ በመምህሩ አጋፋሪነት እንዲሁም በደብሩ የሰበካ ጉባኤ አካላት እና በደብሩ ካህናት አማከኝነት በመሰከረም 19/1974 ዓ/ም  እውቅና ተሰጥቶት የደብረ ምህረት አቡን ቤት ቅዱስ ገብርኤል ሃይማኖተ አበው ተብሎ በይፋ ተመሰረተ፡፡ሃይማኖተ አበው በመባል ምስረታውን ያገኘው ሰንበት ት/ቤታችን  ብዙ አበረታች ስራዎችን ማከናወን ችሏል ፡፡መንፈሳዊ ትምህርትንም የጉባኤ ቤት ደቀ መዛሙርትን በመስተባበር ለህጻናት ፤ለወጣቶች ፤እንዲሁም በአካባቢው ለነበሩት እማት እና አበው እንዲሰጥ ያደርግ ነበር ፡፡በዚህም ሰፊ እውቅና ያገኘ ሲሆን የአካባቢው ሕብረተሰብም ልጆቹን ወደ ሃይማኖተ

     አበው ሂደው እንዲማሩ በማድረግ ዓይነተኛ አስተዋጽኦ ነበረው ፡፡እንዲህ እያለ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ አደረጀጀቱን እና የአገልግሎት አድማሱን በማስፋት እስከ 1985ዓ/ም ድረስ ቀጠለ በዚህ ጊዜ ግን ከስርዓተ ቤተ ክርስቲያን ዶግማ እና ቀኖና ውጭ የሆኑ እንግዳ ነገሮች መከሰት ጀመሩ በሰንበት ት/ቤቱ የሙዚቃ መሳሪያዎች እንደ ፒያኖ እና ሌሎችንም ከመጠቀም ጀምሮ በጠንካራ ኦርቶዶክሳዊነታቸው ይታወቁ የነበሩት የሰንበት ት/ቤታችን ትንታግ አገልጋዮች ሳይቀሩ ምንፍቅናን በሰንበት ት/ቤቱ በይፋ ያስተምሩ ጀመር ፡፡በዚህ እንግዳ ትምህርት ግራ የተጋቡት የደብሩ አገልጋዮች መጀመሪያ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶችን በመምከር ቀጥሎም በማስጠንቀቅ እንዲመለሱ እና የአባቶቻቸውን አሰረ ፍኖት እንዲከተሉ ከቅሰጣ ተገብር እንዲቆጠቡ ብዙ ጥረው ነበር ፡፡እንኳን ከድርጊታቸው ሊታቀቡ ቀርቶ መንፈሳዊ ትምህርት ለመማር እና ስለ እናት ቤተ ክርስቲያናቸው ለማወቅ የመጡትን ሳይቀሩ በመቀሰጥ ከእነርሱ ጎራ ለመቀላቀል አብዝተው ይጥሩ ጀመር ይህ አካሄዳቸውም ከደብሩ አገልጋዮች ብቻም ሳይሆን ከአካባቢው ህብረተሰብ መጠነ ሰፊ ውግዘትን አስከትሎባቸዋል ፡፡በዚህም ሳቢያ ህብረተሰቡ ልጆቹን ወደ ሰንበት ት/ቤቱ ከመላክ የተቆጠበ ሲሆን አያይዞም በቤተ ክርስቲያን ተጠልለው የምንፍቅና ተግባር የሚራምዱትን አካለት ከተቻለ በምክር ካልሆነ ደግሞ ተወግዘው እንዲለዩ ከፍተኛ ውትወታ ያደርግ ጀመር ፡፡ከዚህ በኋላ ነው ብዙዎቹ የሰንበት ት/ቤቱ አመራሮች ድርጊታቸው የተጋለጠባቸው ስለመሰላቸው ካህናቱን እና የአካባቢውን ማህበረሰብ በመስደብ እና በማበጠልተል በራሳቸው ጊዜ ጥለው የወጡት ከፊሎች ደግሞ በካህናት አባቶች ፍጹም አልመለስ በማለታቸው ተውግዘው ተለይተዋል ፡፡በሰንበት ት/ቤቱ የምንፍቅና ድርጊት ተዋናይ ያልነበሩ ጥቂት አባላት የተገኙ ሲሆን የሰንበት ት/ቤቱን ህልውና ማስቀጠል ግን አልተቻላቸውም ፡፡በእርግጥ ላለማስቀጠላቸው የእነርሱ ደክመት ብቻ ሳይሆን እንደዛ በመልካም ዓይን ሲያዩት ብሎም በእውቀታቸው በገንዘበቸው እና በጉልበታቸው ጭምርት ያግዙት የነበሩት የአካባቢው ማህበረሰብ እና ካህናት አገልጋዮች ፊታቸውን በማዞራቸው ጭምርት ነበር ፡፡ስልሆነም ሰንበት ት/ቤቱ ከ1987 እስከ 1991ዓ/ም ህልውናው አክትሞ መረጃዎቹ እና ንበረቶቹ አንዳንድ ኃላፊነት በማይሰማቸው አካላት ተዘርፈው ኦና ሆኖ ቀርቶ ነበር ፡፡ከዚህ ላይ መታለፍ የሌለበት ግን ከአሰበ ተፈሪ ብዙ የሰንበት ት/ቤት ልምድ አካብቶ የነበረው ሲሳይ የተባለ አንድ ወንድም ቤተሰቦቹን ለመጠየቅ ውደ ጎንደር መጥቶ ነበር እና ጎንደር በቆየባቸው ጥቂት ዓመታት ማለትም 1988 እስከ 1990ዓ/ም ህጻናትን እንደገና በማሰባሰብ ይበል የሚባል እንቅስቃሴ አድርጎ ነበር ፡፡
እንደዛ መልካም ስም የነበረው ሰንበት ት/ቤት ፤በማህበረሰቡ የላቀ ተቀባይነት የነበረው ሰንበት ትምህርት ቤት ፤ከህጻናቱ እና ከወጣቱ አልፎ በእድሜ የገፉትን ሰዎች ሳይቀሩ በተጠናከረ መልኩ የወንጌል አገልግሎት ይሰጥ የነበረው ሰንበት ት/ቤት ፤ቀሳጢያን ሰርገው በመግባት እና በርካታ ልጆችን በመበረዝ የሰንበት ት/ቤቱ ህልውና እንዲንኮታኮት ቢያደርጉም ልጆቹ የትም ተበትነው እንዲቀሩ የማይፈልገው እግዚአብሔር እንደገና ሰንበት ት/ቤቱ እንዲያንሰራራ እና በሁለት እግሩ እንዲቆም አደረገ፡፡ለሰንበት ት/ቤቱ ትንሳኤም ዓይነተኛ ድርሻ የነበራቸው የማኅበረ ቅዱሳን አባላት ነበሩ፡፡ እነዚህ የማኅበሩ አባላት በተለይም ሴቶች አንድም የማኅበራቸውን የጎንደር ማዕከል በማጠነከር በሌላም በታሪክም ቢሆን በተወሰነ መልኩ ወደሚውቁት ሰንበት ት/ቤት በመምጣት የአካባቢውን ወጣት በዛም በዚህም ብሎ በማሰባሰብ ለሰንበት ት/ቤቱ እንደገና ነፍስ ዘሩበት እነዚሁ የቤ/ክ ልጆች ለወጣቶች መዝሙር በማስጠናት ፤መሰረታዊ የቤተ ክርስቲያን ት/ት (ኮርስ) በመስጠት ልምዳቸውን በማካፈል ብሎም አንዳንድ ኃላፊነት በማይሰማቸው አካላት የተዘረፉትን ንበረቶች ገዝተው በመተካት ፤ኮሚቴ በማዋቀር ፤የአገልግሎት
ክፍሎችን በማደራጀት ሰንበት ት/ቤቱን በጥቂት ዓመታት ውስጥ ወደቀድሞ ዝናው መለሱት፡፡አባላቱም በዛ፤ አደረጃጀቱም የተጠናከረ ሆነ፤ ፊተቸውን አዙረው የነበሩት የደበሩ አገልጋዮች እና የአካባቢው ማህበረሰብም የሰንበት ት/ቤቱን አኳኋን አይተው ፊታቸውን መለሱ ፤የሰ/ጎ/ዞን ሀ/ ስብከትም የሰንበት ት/ቤቱን በጎ እንቅስቃሴ በመመልከት 20 የሚደረሱ መጽሐፍ ቅዱስን ለገሰ ፤ሰበካ ጉባኤውም ምንም፣ እንኳን ከሰንበቴ ቤት አዳራሻ ወጥቶ የማያውቀውን ሰንበት ት/ቤት የተሻለ የሚባለውን ሰንበቴ ቤት እንዲያኝ አደረገ፡፡ብሎም አልባሳት እና ድምጽ ማጎያን ጨምሮ ለሰንበት ት/ቤቱ አገልግሎት የሚውሉ የተለያዩ ቅሳቁሶችን በጀት በመመደብ በተወሰነ መጠን አሟላ ፡፡በአጠቃላይ ሰንበት ት/ቤቱ ከ1990ዎቹ መጀመሪያ አንስቶ እስካሁኗ ሰዓት ድረስ በሁሉም መስክ ማለት ይቻላል ይበል የሚያሰኝ እንቅስቃሴ እያከናወነ ይገኛል፡፡እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ሰንበት ት/ቤታችን በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እያከነወነቸው ያሉ አበረታች ተግባራትን በሚቀጥለው ጊዜ በደንብ የምናቀርብ መሆኑን እንገልጻለን፡፡እሰከዚያው ግን ይቆየን …….ያቆየን
‹‹ ወስብሐት ለእግዚአብሔር ››


No comments:

Post a Comment