Wednesday, May 8, 2013

የግንቦት ልደታ ለማርያም ክብረ በዓል


                                                
የእመቤታችን በዓላት
በቀደመዉ ዘመን በዘመነ ብሉይ ‹‹የቤተ መቅደስ መታደስ በዓል››ይከበር እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ያስረዳል፡፡ይህ በዓል እስከ ጌታችን ዘመንም ይከበር ነበር፡፡(ዮሐ 10-22)በሐዲስ ኪዳን እዉነተኛ የእግዚአብሔር ማደሪያ ቤተ መቅደስ ለሆነችዉ እመቤታችን በስሟ በ ዓል ሊደረግላት ይገባል‹‹የጻድቅ መታሰቢያ ለዘላለም ይኖራል›› እንዳለ ቅዱስ ዳዊት መዝ 111-7
በተ አምረ ማርያም ላይ በዝርዝር እንደተቀመጠዉ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሠላሳ ሦስት በዓላት አሏት ፡፡ከእነዚህ በ ዓላት ሁሉ አስበልጣ የምትወደዉ በዓለ ልደቷን እንደሆነ በአጼ ዘርዓ ያዕቆብ ዘመነ መንግስት ከዐረብኛ ወደ ግእዝ በተተረጎመዉ እመቤታችን በተለያዩ ሀገራት ያደረገቻችዉን ገቢረ ተአምራት በኢትዮጵያ ከተፈጸሙት ጋር አካቶ የያዘዉ ተአምረ ማርያም በዝርዝር ያስረዳል፡፡
ልደቷ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ከሌለ ተቀባይነት እንዴት ይኖረዋል
በመጽሐፍ ቅዱስ ያልተካተቱና ምሉዕነት የሌላቸዉ ታሪኮች በአዋልደ መጻሕፍት እንደሚሟሉ ራሱ መጽሐፍ ቅዱስ ያስረዳል ለምሳሌ ስለ ቅዱስ ዳዊት የሚናገረዉ መጽሐፈ ዜና መዋዕል ‹‹የንጉሡም የዳዊት የፊተኛዉና የኋለኛዉ ነገር በነቢዩ በናታን ታሪክ እንዲሁም በባለ ራእዩም በጋድ ታሪክ ላይ ተጽፏል›› 1ኛ ዜና 29-29
የእመቤታችን ታሪክ
የእመቤታችን ወላጆች በአብዛኛዉ አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ‹‹ሀና››እና ኢያቄም/ዮአኪን በሚለዉ ስም የሚጠሩ ሲሆን ሀና በቤተልሔም ተወልዳ እንዳደገች ታሪክ ያስረዳል፡፡በናዝሬት ገሊላ ለመሥዋዕት የሚሆኑ በጎች የሚያቀርብ እንዲሁም እረኛ
የነበረዉን ኢያቄምንም አግብታለች፡፡ቅድስት ሀና ወደ ቤተ መቅደስ ስትሔድ አርጋብን አይታ ታለቅስ ነበር፡፡ከብዙ ልመና በኋላ ቅድስት ድንግል ማርያምን ግንቦት አንድ ቀን በደብረ ሊባኖስ ወልደዋል፡፡
ስለ ሃና መካንነት ወደ ቤተ መቅደስ ሄደዉ መባዕ ሲያቀርቡ ካህኑ ያልተቀበላቸዉ መሆኑን በብስራተ መልአክ ልጅ እንደሚወልዱ እንደተነገራቸዉ በእኛ ቤተ ክርስቲያን የሚተረከዉና በሌሎች ኦርቶዶክሳዊያን አብያተ ክርስቲያናት የሚነገረዉ ታሪክ ተመሳሳይ ነዉ፡፡
እመቤታችን የት ተወለደች?
እመቤታችን ስለተወለደችበት ስፍራ በዓለም የተለያዩ ሀሳቦች ይስተጋባሉ፡፡ሌላዉ ቀርቶ በዶግማ አንድነት ባላቸዉ አኃት አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ በእንዲህ ዓይነት ታሪክ ነክ ጉዳዮች ላይ ልዩነት መኖራቸዉ የተለመደ ክስተት ነዉ፡፡የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሁለት ሀሳቦች የሚያነሱ ሲሆን አንደኛዉ‹‹ድንግል ማርያም ብስራተ መልአክ በሰማችበት ናዝሬት ተወልዳለች››የሚል ነዉ፡፡ሁለተኛዉ ሀሳብ ደግሞ‹‹ከሦስተኛዉ ክ/ዘመን ወዲህ የማርያም መግቢያ ተብሎ በሚታወቀዉ ከኢየሩሳሌም የቅ/ሀና የክሩሲድ ቤተ ክርስቲያን በታች ነዉ የተወለደችዉ የሚል ነዉ፡፡
የግብጽ ስንክሳር የእመቤታችን የትዉልድ ስፍራ በናዝሬት ነዉ ይላል፡፡የኢትዮጵያ ስንክሳር ግን በቀደምትነታቸዉ ተጠብቀዉ የቆዩ ከመሆናቸዉ አንጻር ተአማኒነታቸዉ የጎላ መሆኑን ያሳያል፡፡በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መጻሕፍት የእመቤታችን የትዉልድ ስፍራ ሊባኖስ የተባለዉ ተራራማ ሀገር ነዉ፡፡ሊባኖስ ከገሊላ በስተ ሰሜንና ከፍንቄ በ ስተ ምስራቅ ይገኛል፡፡‹‹ሙሽራየ ሆይ ከሊባኖስ ከእኔ ጋር ነይ››የሚለዉ ቃለ ትንቢት ምስጢርም የአመቤታችን መካነ ልደት የሊባኖስ ተራራ ስለመሆኑ የሚያጠይቅ እንደሆነ ምስክርነታቸዉ የታመነ የቤተ ክርስቲያን ሊቃዉንት ያስረዳሉ፡፡መኃ 4-7
የልደታ ለማርያም በዓል መቸ ነዉ?
እንደተወለደችበት ሥፍራ የእመቤታችን የልደት ቀን እንዲሁ አወዛጋቢ ነዉ፡፡ በ 6ኛዉ ና7ኛዉ መቶ/ክ/ዘመን ነዉ የሚሉ የተለያዩ ሃሳቦች የተጻፉ ሲሆን Encyclopaedic of Christian antiquities ደግሞ በ431 ዓ/ም ከተካሄደዉና ንስጥሮስ ከተወገዘበት ከጉባኤ ኤፌሶን በኋላ ነዉ ይላል፡፡በዓለም ቅዱሳንን የሚያከብሩ አብያተ ክርስቲያናት የቅዱሳንን በዓለ   እረፍታቸዉን የሚያከብሩ ሲሆን ልደታቸዉ የሚከበረዉም በሦስተኛ ደረጃ የመጥምቀ መለኮት ቅ/ ዮሐንስ፤በሁለተኛ ደረጃ የእመቤታችን ቅ/ድንግል ማርያም ልደት ነዉ፡፡በአንደኛ ደረጃ ለስም አጠራሩ ክብር ይግባዉና የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት ነዉ፡፡
የአመቤታችን ልደት በምዕራባዊያን አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ ኬክ በመጋገር፡የአመቤታችን ትንሽ ሀዉልት በማቆም ዐስር ሻማዎችን በማብራት ያከብራሉ፡፡
የድንግል ማርያም ልደት ለምን ይከበራል?
&  ስለ መጥምቁ ዮሐንስ ልደት በመልአኩ ቅዱስ ገብርኤል አንደበት‹‹በመወለዱ ብዙዎች ደስ ይላቸዋል››በማለት ተነግሯል(ሉቃ 1-14)ምክንያቱም ቅ/ዮሐንስ የጌታ መንገድ ጠራጊ የአዋጅ ነጋሪ በመሆኑ ነዉ፡፡የቅዱስ ዮሐንስ መወለድ ለብዙዎች ደስታ ምክንያት ከሆነ የድንግል ማርያም ልደት ምንኛ የሚያስደስት ይሆን፡፡ስለሆነም ከጌታ ቀን ቀጥሎ የምንደሰትበት ትልቁ ቀን የእርሷ የልደት ቀን ነዉ፡፡
&  የቀርጤሱ ቅ/እንድርያስ ስለ ከበረ ልደቷ እንዲህ ብሏል‹‹ይህ በዓል በሐዲስና በብሉይ ኪዳን መካከል መገኛ ሆነ፡፡ምስሌዎቹ በ እዉነታ፣ አሮጌዉ በአዲስ ቃል ኪዳን ተተኩ፡፡ፍጥረት ሁሉ በደስታ ይዘምራል የዚህን ቀንም ደስታ ይካፈላል፡፡ይህ መቅደሱን የሰራበት ዕለት ነዉ፡፡ይህ ዕለት ትልቅ ህንፃ የታነጸበትና ፍጡር የፈጣሪ ማደሪያ ለመሆን የተዘጋጀበት ዕለት ነዉ፡፡››ብሏል
&  እመቤታችን  ለፀሐዩ መምጣት የተዘረጋች ሰማይ፡በቅድመ አያቶቿ በነ ቴክታና ጰጥሪቃ ህልም እንደታየችዉ በሌሊት የምታበራ ጨረቃ የብሉይ ኪዳን ማብቂያ የሐዲስ ኪዳን መጀመሪያ ናትና ልደቷ ለሰዉ ልጅ ሁሉ ደስታ ነዉ፡፡
& ነቢያት በብዙ ሕብረ አምሳል የተናገሩላት‹‹መሰረቶቿ የተቀደሱ ተራራዎች ናቸዉ››‹‹ከእሴይ ስር በትር ትወጣለች አበባዋም ከግንዱ ይወጣል››‹‹ሙሽራየ ሆይ ከሊባኖስ ነይ›.ብለዉ ተናገሩላት ቅ/ድ/ማርያም ልደቷ የትንቢታቸዉ ፍፃሜ ነዉና ታላቅ ደስታቸዉ ነዉ፡፡(መዝ86-1 ኢሳ 11-1)
&  በዓለም ላይ የብዙ ታዋቂ ሰዎች ልደት ከሞቱም በኋላም ጭምር በታላቅ ድምቀት ይከበራል ታዋቂ ያልሆኑ ሰዎች ልደትም እንዲሁ ይታሰባል ለሰዉ ልጅ መዳን ምክንያት የሆነች የአምላክ እናት የተወለደችበት ቀን ምንኛ ሊከበር ይገባዉ ይሆን!
የግንቦት ልደታ በዓል አከባበር
በቤተ ክርስቲያናችን ትዉፊት መሰረት ሃና እና ኢያቄም ከአይሁድ ለማምለጥ ተሰደዉ በአድባረ ሊባኖስ ስር  እመቤታችንን ወለዱ በወቅቱ ከቤት የወጡት ለሽሽት ነበርና ስንቅ ስላልያዙ ምግባቸዉ‹‹ንፍሮና ጥራጥሬ›› ነበር፡፡ይኼንን ትዉፊት በመያዝ በዓሉ ከቤት ዉጭ ንፍሮ እየተበላ ይከበራል፡፡ሆኖም በበጎ ነገሮች ሰበብ ክፉ ዓላማዉን ማስፈጸም የሚፈልገዉ ዲያቢሎስ በማር መሃል መርዝን ከሚጨምርባቸዉ መንፈሳዊያት በዓላት አንዱ የግንቦት ልደታ የእመቤታችን በዓል ነዉ፡፡አንዳንዶች በድፍረት ለአድባር ለዉጋር ነዉ፣ቆሌዉን ለመለመን ነዉ፣ እያሉ ንፍሮ የሚበትኑ፣ቡና የሚረጩ፣ቂቤ የሚቀቡ፣የከብት ደም የሚያፈሱ፣  እነዚህ በእርግጥም ጣዖት አምላኪዎች ናቸዉ፡፡እኛም ከእንደዚ ዓይነቶቹ አሰናካዮች በመለየት ይኼንን ታላቅ በዓል በተገባና በተረዳ ነገር እንድናከብረዉ የ እመቤታችን ረድኤት በረከት አይለየን፡፡
                         ወስብሐት ለእግዚአብሔር
                                                                                       ምንጭ ሐመር 20ኛ ዓመት ቁጥር 1

1 comment:

  1. በጣም ደስ ይላል… እግዚአብሔር ይስጥልን

    ReplyDelete