Wednesday, May 8, 2013

ለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ልደት በዓል እንኳን አደረሳችሁ!!!

እንኳን ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም ዓመታዊ የልደት መታሰቢያ በዓል ዋዜማ በሰላም አደረሰን አደረሳችሁ አሜን።
“ኦ ድንግል አኮ በፍትወተ ደነስ ዘተፀነስኪ አላ በሩካቤ ዘበሕግ እምሐና ወኢያቄም ተወለድኪ”
ሙሽራዬ ሆይ ከሊባኖስ ከእኔ ጋር ነይ : ከሊባኖስ ከእኔ ጋር ነይ ። (መኃ 4:8 ) 
+++ድንግል ሆይ በኃጢአት ፍትወት የተፀነስሽ አይደለም ፤
በሕግ በሆነ ሩካቤ ከሐና ከኢያቄም ተወለድሽ እንጂ

አባ ሕርያቆስ በቅዳሴ ማርያም +++ ስብሃት ለኪ ማርያም እሙ ለፀሃየ ጽድቅ ለአብ ሙሽራው ለወልድ ወላዲቱለመንፈስቅዱስ ጽርሃ ቤቱ ተፈስሂ ደስ ይበልሽ እመቤታችን እግዝትእነ ማርያም በተፀነሰች በ9 ወር ከአምስት ቀን የግንቦት መባቻ ዕለት ግንቦት 1 ተወለደች። 
መዝሙረኛው ሶሎሞን አባቱ ዳዊት በራዕይ ያያትና በነገስታትና በነብያት ስትጠበቅ ለኖረችው ለቅድስት ድንግል ማርያም የተናገረው ትንቢት ነበር :: ይህም ትንቢት ልደቷን የተመለከተ ነው :: የተወለደችው እናቷ በስደት እያለች በሊባኖስ ተራራ ላይ ነውና። 

እመቤታችን የተወለደች እለት አባቷ ኢያቄምና እናቷ ሀና ከመጠን በላይ ተደሰቱ። የተወለደችበት ቦታ ግን በስደት በተራራ ላይ በመሆኑ ሀና በድሎት አልታረሰችም። ዘመድ አዝማድ ሊጠይቅ ሲመጣ ሁሉም የአራስ ጥሪ ያለውን ይዞ ሲያመጣ አንዲት ቅን ልቦና የነበራት ነገር ግን እጅግ ድሀ የሆነች ሴት በቤቷ ያለውን ጥራጥሬ አሟጣ ሰብስባ ቀቅላ ንፍሮ አድርጋ ይዛላት ሄዳ ነበር :: አራስ ጥሪው የችግረኛ ቢሆንም ያላትን በማድረጓ እግዚአብሔር ከሌሎች ይልቅ የርሷን ስጦታ ወዶላታል :: ይህም በወንጌል ታሪኳ የተጻፈላትን የዚያችን ሁለት ሳንቲም ሰጥታ የሄደችውን ድሀ መበለት ታሪክ ያስታውሰናል።

እኛም የእመቤታችንን ልደት ለማስታወስ ቤት ውስጥ በተመቻቸው ቦታ ሳይሆን ውጪ ሆነን ንፍሮ ቀቅለን: ምንጣፍ አንጥፈን እናስታውሰዋለን - በግንቦት ልደታ
ዮም ፍስሃ ሆነ !!!! እነሆ ድንግል ተወለደች ለአዳም ዘር ሁሉ ብርሃን ሆነ ያመናችሁ ሁሉ ኑ በድግል ደስ ይበለን።

ለመላው የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ልጆች በሙሉ እንኳን ለዚህ ታላቅ ክብረ በአል ዋዜማ በሰላም አደረሳችሁ። 
ለአባ ሕርያቆስ ፤ለቅዱስ ኤፍሬም ፤ለቅዱስ ያሬድ ፤ ለአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ የተገለጸች ዕመቤታችን እኛንም በበረከት እና በረድኤት ትጎብኘን ፤ ከልጅዋ ከወዳጅዋ ከመድኃኔዓለም ዘንድ ታማልደን።!!!

No comments:

Post a Comment