Monday, March 18, 2013

ጾም ለምን?(ክፍል አንድ)


ጾም ለምን?(ክፍል አንድ)
      የጾም ጥቅሙና አገልግሎቱ በጥንት አበዉ ጀምሮ በጎላ በተረዳ ነገር የታወቀ ነዉ፡፡ሆኖም በዘመናችን ብዙ ሰዎች ስለምን እንደሚጾሙ ጠንቅቀዉ ካለመረዳታቸዉ ይመስላል ጾም ከ እህል ከዉሀ ተከልክሎ ለተወሰኑ ሰዓታት መቆየት ከጥሉላት መባልዕት ብቻ መለየት እንደሆነ ያስባሉ፡፡‹‹ጾም አከሳኝ››በማለት ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡የጾም ዓላማ ይህ ይመስላቸዋል፡፡እንዲህ ግን አይደለም፡፡ሰዉ ለስርየተ አበሳ ዋጋዉ እንዲበዛለት፤የፈቲዉ ጾር ያደክም ዘንድ፤ስጋ ለነባቢት ነፍስ ትታዘዝ ዘንድ ይጾማልና፡፡ስለሆነም የጾምን ጥቅም እንደሚከተለዉ በዝርዝር እናቀርባለን፡፡
ጾም ፈቃደ ስጋን ለነባቢት ነፍስ ለማስገዛት ይጠቅማል
ፈቃደ ስጋና ፈቃደ ነፍስ ሁልጊዜ እርስ በ እርሳቸዉ ይቀዋወማሉ፡፡አንዱ በአንዱ ላይ የበላይ በመሆን ፈቃዱን ሊያሰራዉ ያሻል፡፡ቅዱስ ጳዉሎስ‹‹በፈቃደ ነፍስ ጸንታችሁ ኑሩ ፈቃደ ስጋችሁን ግን አትስሩ ፡፡ስጋ ነፍስ ልትሰራዉ የማትወደዉን ይወዳልና ነፍስም ስጋ ሊሰራዉ የማይወደዉን ትወዳለችና እርስ በእርሳቸዉም ይጣላሉ ፡፡››በማለት ተናግሯል፡፡ገላ 5-16፡፡ስለሆነም ፈቃደ ስጋ በፈቃደ ነፍስ ላይ ኃይል እንዳይኖረዉ መጾም ፤መጸለይ፤መመጽወት ያስፈልጋል፡፡ሰዉ ፈቃዳተ ነፍሱን በመፈጸሙ ከፈጣሪ ከአምላኩ ጋር ህብረት አንድነት ይኖረዋል፡፡ከፈተናና ከመከራ ይድናል፡፡የፈለገዉንም ያገኛል ፡፡ለፈቃደ ስጋዉ ከ ተገዛ ግን ራሱን የኃጢያት ባሪያ ያደርገዋል ሮሜ 7-10
ጾም እግዚአብሔርን ለመለመንና ከእርሱ መልካም የሆነዉን ነገር ለመቀበል ይጠቅማል
     መጾም ከእግዚአብሔር የሚገኘዉን ጸጋና በረከት ይቅርታን ምህረትን ለማጎናጸፍ ይጠቅማል፡፡ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ለምኑ ይሰጣችኋል ፡መዝጊያ አንኳኩ ይከፈትላችኋል፤የሚለምን ሁሉ ይቀበላልና የሚፈልግም ያገኛል››ብሏል፡፡ማቴ 7-7 የቀደምት አበዉን ሕይወት ስንመለከት ጾመዉ ያፈሩበት ጊዜ እንዳልነበር እንረዳለን ፡፡ለአብነት የሚከተሉትን እናያለን፡፡
    Ω ሊቀ ነቢያት ሙሴ
በደብረ ሲና 40 ማዓልት እና ሌሊት ከጾመ በኋላ በግብር አምላካዊ የተጻፉ ዐስርቱ ቃላትን፤ሕገ ኦሪትን፤ታቦተ ጽዮንን ተቀብሏል፡፡
     Ω ቆርነሌዎስ
ቆርነሌዎስ የፍልስጤም ክፍል በምትሆን በቂሳርያ መቶ አለቃ ሆኖ ተሾመ ከዋክብት ሲያመልክ የነበረ ሰዉ ነዉ፡፡በኋላም የሐዋርያትን የጃቸዉን ተአምራት፤የስብከታቸዉን ዜና ሰምቶ ወዲያዉኑ ለ አማልክት መስገድን ተወ ከዚህም በኋላ የሚጸልይ፤የሚጾም፤ለችግረኞች የሚመጸዉት ሆነ፡፡ቸር ይቅር ባይ እግዚአብሔርም ይቅር ብሎት በ ሐዋርያዉ ቅ/ጴጥሮስ አማካይነት ቆርነሌወስ እስከ ቤተሰቦቹ ፤እንደዚሁም በአካባቢዉ ከ ነበሩት ብዝዎቹ አምነዉ ተጠምቀዋል፡፡የሐዋ 10-1 እነ ነቢዩ ዳንኤል በምርኮ እያሉ የባቢሎን ቤተ መንግስት ጮማና ጠጅ ሳያጓጓቸዉ ጥራጥሬና ዉሃ ብቻ እየተመገቡ አስር ቀናት ጾሙ፡፡ከንጉሱ ገበታ ከተመገቡት ብላቴኖች ሁሉ ይልቅ ፊታቸዉ አምሮና ስጋቸዉ ወፍሮ ታየ ፡፡ስጋ ባለመባላታቸዉ አልከሱም አልጠቆሩም ፡፡እግዚአብሔር  ለእነዚህ ባላቴኖች በትምህርትና በጥበብ ሁሉ ማስተዋልን ሰጣቸዉ ፡፡ዳን 1-8 -1
   Ω ቅዱሳን ሐዋርያት
የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ሐዋርያት ጾመዉ የመንፈስ ቅዱስ ጸጋ እንደተቀበሉ ቅዱስ ሉቃስ ጽፎልናል፡፡የሐዋ 13-1፡፤ቅ/ጳዉሎስም አብዛኛዉን ጊዜ በጾም ያሳልፍ የነበረዉ መልካም ነገርን ከእግዚአብሔርን ለመቀበል ነዉ፡፡
ጾም ኀዘንን ለመግለጽ ይጠቅማል
ጾም ስለራሳችን እና ስለሌሎች(ስለተሰደዱ፤ ስለታሰሩ፤ስለተጨነቁ፤በጦርነት ስለሚሰቃዩ፤በደዌ ዳኛና በአልጋ ቁራኛ ስለተያዙ ወገኖች)ለማዘንና ከእግዚአብሔር ምህረትን ለመለመን ይጠቅማል፡፤የቀደሙትን አባቶች አነዋወር ስንመለከት ኀዘን መከራ ባገኛቸዉ ጊዜ ሁሉ ማሶገጃ መፍትሔ አድርገዉ የሚወስዱት ጾምና ጸሎትን ነበር፡፡ለአብነት የሚከተሉትን አንመልከት፡፡
         ûከክርስቶስ ልደት 400 ዓመት በፊት ይኖር የነበረ ነህምያ የወገኖቹን ዉርደትና መከራ የኢየሩሳሌም የቅጥሮቿ መፍረስ የበሮቿ መቃጠል በሰማ ጊዜ ኀዘኑን የገለጠዉ በጾምና በጸሎት ነበር፡፡
          ûዕዝራም በምርኮ ስለነበሩት ወገኖቹ ኃጢአትና በደል ባለቀሰ ጊዜ ኀዘኑን የገለጠዉ በጾም ነበር፡፡ዕዝ 10-6
          ûአይሁድ በንጉሱ በ አርጤክስ ዘመን በሐማ ተንኮል የሞት አዋጅ በታወጀባቸዉ ጊዜ ኀዘናቸዉን የገለጡት በጾም ነዉ፡፡ጾምና ጸሎታቸዉ በ እግዚአብሔር ፊት ተቀባይነት አግኝቶ በመርዶክዮስ ፋንታ ሐማ ተሰቀለ አይሁድም ከታወጀባቸዉ የሞት አዋጅ ነጻመዉጣትም ችለዋል፡፡
            ሐዋርያዉ ቅዱስ ያዕቆብ ‹‹እናንተ ኃጢአተኞች እጃችሁን አንሱ ሁለት አሳብም ያላችሁ እናንተ ልባችሁን አጥሩ ፡፡ተጨነቁ ና እዘኑ አልቅሱም ሳቃችሁ ወደ ኀዘን ደስታችሁም ወድትካዜ ይለወጥ ››ይላል ፡፡ያዕ 4-8-9 በ ኢዮኤልም እንዲህ ተባሏል‹‹በጽዮን መለከትን ንፉ ጾምን ቀድሱ ጉባኤንም አዉጁ ሕዝብንም አከማችሁ ማኅበሩንም ቀድሱ ጉባኤዉንም አዉጁ ሕዝቡን አከማችቹ ሙሽራዉ ከእልፍኝ ሙሽራይቱም ከጫጉላዋ ይዉጡ የእግዚአብሔርም አገልጋዮች ካህናት ከወለሉና ከመሰዊያዉ መካከል እያለቀሱ አቤቱ ለህዝብህ ራራ ይበሉ፡፡››ኢዩ 2-15
          ጾም ድካምን አዉቆ ሰዉነትን ቅድመ እግዚአብሔር ለማዋረድ ዋነኛ መሳሪያ ነዉ
በአገር ላይ ያልታሰበ ፈተና ሲያጋጥም ሕዝብ እንዲጾም እንዲጸልይ በእግዚአብሔር ፊት እራሱን እንዲያዋርድ ጾም ይታወጃል ፡፡ምክነያቱም ጾም ወደ እግዚ አብሔር ልመና የማቅረቢያና የይቅርታ መጠየቂያ መንገድ ስለሆነ ራስን በ እግዚአብሔር ፊት በጾም ማዋረድ ክብር ነዉ፡፡‹‹እንግዲህ በጊዜዉ ከፍ እንዲያደርጓችሁ ከ ኃይለኛዉ ካግዚአብሔር እጅ በታች ራሳችሁን አዋርዱ››እንዲል ቅዱስ ጴጥሮስ 1ኛ ጴጥ 5-6፡፡ራስን ማዋረድ መከራንና ትዕቢትን አርቆ ክብርን ያለብሳል፡፡
ጸም ድካማችን እንድንገነዘብ እኛነታችን እንድናዉቅ ይረዳናል፡፡ድካምንም ማወቅ ለትሩፋት መሰረት መጀመሪያ ናት፡፡ከእግዚአብሔር ጋር መልካም ግንኙነት የነበራቸዉ አባቶች ሰዉነታቸዉን አዋረዱ፡፡እግዚአብሔርም ልመናቸዉን ሰማቸዉ፡፡የፈለጉትንም ነገር ሰጣቸዉ፡፡ስለዚህም ዕዝራ‹‹በፈጣሪያችን ፊት እናዋርድ ዘንድ ጎዳናችን ያቀናልን ዘንድ ለልጆቻችንናለፍጥረቱም ሁሉ ጎዳናቸዉን ያቀናልን ዘንድ አኀዋ በሚባል ወንዝ ጾምን እንጹም ብየ አዋጅ ነገርኩኝ ስለዚህም ነገር ጾምን ወደ እግዚአብሔር ለመንን እርሱም ተለመነን››አለ  ዕዝ 8-21-23፡፡እንዲሁም ነቢዩ ዳንኤል በጾም ሰዉነቱን በ ፈጣሪዉ ፊት በማዋረዱ ልመናዉ ተሰምቶለታል
 ፡፡ይሄዉም ሊታወቅ መልአኩ በሚስፈራ ግርማ ተገልጦ‹‹ዳንኤል ሆይ አትፍራ ልብህ ያስተዉል ዘንድ ሰዉነትም በ አምላክ ፊት ይዋረድ ዘንድ ካደረክበት ከመጀመሪዉ ቀን ጀምሮ ቃልህ ተሰምቷል እኔም ስለቃልህ መጥቻለሁ››ብሎታል ዳን 10-12

                         ብሒለ  አበዉ
 & ‹‹ብዙ ከመብላትና ብዙ ከመጠጣት የማይከለከል ሰዉ ሰይጣነ ዝሙትን ድል አይነሳዉም፡፡››(ማር ይስሀቅ)
 & ‹‹መመጽወትና መጾም ለነፍስ ህይወትን ለስጋ ጤንነትን ይሰጣል፡፡››(አንጋረ ፈላስፋ)
 & ‹‹ያለ ጸሎት መንፋሰዊ ነኝ የሚል ሰዉ እሳት መካከል ገብቶ የሚጫወትን የ እሳት እራትን ይመስላል፡፡››(ማር ይስሐቅ)
 & ‹‹ልጀ ሆይ አንተ በራስህ ላይ ስትፍረድ እግዚአብሔር ፍርዱን ያነሳልሃል አንተ በራሰህ ላይ ባትፈርድ ግን  እግዚአብሔር  ይፈርድብሀል(ታላቁ መቃሪዮስ)
 & ‹‹በወንድሙ ወድቀት የሚደሰት ሰዉ ተመሳሳይ ወድቀት ይጠብቀዋል››(ቅዱስ ኤፍሬም)
 & ‹‹የወንድምህን ኃጢአት መሸፈንና ያእርሱን ኃጢአት እንደራስህ አድርግህ በእርሱ ፋንታ መሞት ካልቻልክ ቢያንስ ስለ ኃጢአቱ አትፍረድበት››(ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ)
 & ‹‹በእግዚአብሔር ዘንድ ባለሟልነትን ታገኝ ዘንድ ታገስ››(ማር ይስሐቅ)
                          ስንት ይሆን ኪሎየ
           በሕይወት መስመር ላይ በኑሮ ጎዳና
          ጉዞየ ከሆነ ዉሃ አልባ ደመና
           ዘንግቸ ከወጣሁ የፍቅር እንጎቻ
          ተስተካክሎ ቢቆም ልብስና ስጋየ
           በነፍስ ሚዛን ላይ ስንት ይሆን ኪሎየ
                                  ምንጭ፤-ሐመር 17ኛ ዓመት ቁ 2 ግንቦት -ሰኔ 2001ዓ/ም
        
ወስብሐት ለ እግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክብር!!

No comments:

Post a Comment